ለህብረተሰቡ የሚቀርበው ንፁህ የመጠጥ ውሃ በአገር አቀፍ የጥራት መለኪያ መስፈርት ውስጥ ማለፍ አለበት ተባለ

130
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አማካኝነት ለህብረተሰቡ የሚቀርበው ንፁህ የመጠጥ ውሃ  በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና መስፈርት ውስጥ ማለፍ እንዳለበት የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፌዴሬሽን ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "የአገር አቀፍ የከተሞች የመጠጥ ውሃ ዘርፍ የውሃ ጥራት ሰርተፍኬትና እውቅና መርሃ ግብር " በዛሬው እለት አዲስ አበባ ውስጥ ተካሄዷል። በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በዚሁ ወቅት  እንደተናገሩት ለህብረተሰቡ የሚቀርበው ውሃ ጥራት በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት አማካኝነት መረጋገጥ  እንዳለበት የታመነ በመሆኑ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል። የምዘናው መስፈርቶች እስከ ሃምሳ የሚደርሱ ሲሆኑ ከአላስፈላጊ ኬሚካሎች ጋር የተያያዙና በሰው ጤናና ህይወት ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ተህዋሲያን ነፃ መሆኑን መሰረት ያደረጉ ናቸው። በስነ-ስርዓቱ ላይ የደሴ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ፅህፈት ቤት የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጥቶታል። ፅህፈት ቤቱ አውቅናውን ያገኘው የሚያቀርበው ውሃ ጥራት በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት አንዲመዘን በራሱ ተነሳሽነት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው።  ፅህፈት ቤቱ የጥራት ማረጋገጫ ሲያገኝ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ተመልክቷል። በመላ አገሪቷ 55 ከተሞች የንጹህ መጠጥና ፍሳሽ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውሃ ሃብታቸውን ከማስተዳደርና በተደራሽነት ላይ ከመስራት ባለፈ የሚያቀርቡትን ውሃ ጥራት የማረጋገጥና እውቅና የማግኘት አሰራር ሂደት ውስጥ እስከ መጪው ነሃሴ 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ  መግባት እንዳለባቸውም  ሚኒስትር ዲኤታዋ አሳስበዋል። በስነ-ስርዓቱ ላይ የተሳተፉ የክልል የውሃና ፍሳሽ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ወደ አሰራሩ እንደሚገቡ ገልፀዋል። የሃዋሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፅህፈት ቤት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ፀሃዩ ከተማዋ የላብራቶሪ እቃዎችንና ባለሙያዎችን አሟልቶ  እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከደሴ ከተማ ተሞክሮ በመውሰድ በሚቀጥሉት ወራት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ምዘናውን ለማከናወን ዝግጅት ይደረጋል ብለዋል። በተለይም ቀጣይነት ባለው መልኩ የውሃ ጥራትን የተመለከቱ  ዳታዎችን ከማደራጀት፣ ከመከታተልና አሰራርን ከማዘመን ረገድ ጠቃሚ ልምድ መውሰዳቸውንም ገልፀዋል። የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሃመድ ሙርሲ በበኩላቸው አስካሁን ወደ አሰራሩ ያልገባነው ትልቅ ትኩረት የሰጠነው በተደራሽነት ላይ ስለሆነና በገለልተኛ ተቋም ጥራቱን ለማረጋገጥ  ትኩረት ስላልሰጠን ነው  ሲሉ ተናግረዋል። እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2010ዓ.ም ድረስ በከተማው ሊፈቱ የሚችሉ ክፍተቶችን በመለየትና በመፍታት ወደ አሰራሩ እንገባለን ያሉት ስራ አስኪያጁ ከአካባቢው ውሃ ጫዋማነት ጋር የተያያዘው ችግር ግን እስከ 1 ቢሊዮን ብር የሚጠይቅና ጊዜ የሚፈልግ ነው ብለዋል። በዚህም መሰረት ከተማው በአቅሙ ሊሰራቸው የሚችለውንና ለጤና ጉዳት የሚያመጡ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም