ሶማሊያዊቷ ወጣት የመብት ተማጓች የጀርመንን ሽልማት አሸነፈች

71

ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) ሶማሊያዊቷ  የመብት  ተሟጋችና  በጎ  አድራጊ  የ30 ዓመቷ  ወጣት ኢልዋድ ኤልማን የዘንድሮው 2020 የጀርመንን ሽልማት አሸነፈች።

ኤልዋድ ኤልማን የምትመራው  “የኤልማን  የሠላም ማዕከል”  ድርጅት  “ጠመንጃውን አስቀምጡ ፣ ብዕር ጨብጡ”  ባለው መርህ  ብዙ የቀድሞ  ልጅ ወታደሮችን ሕይወት መቀየሩ ታውቋል።

በሴቶች ላይ የሚደርስ በደልን በተለይም አስገድዶ መድፈርን ለማስቀረትና ተበዳዮችን ለመርዳት ባደረገው ጥረትም ብዙ ሴቶችን ከጥቃት ማዳን፣ የተጠቁትን የተሰበረ ልብ መጠገን በመቻሉ የጀርመኑ  የአፍሪካ  ሸላሚ ድርጅትን  ሽልማት አሸናፊ መሆኗ ተገልጿል።

የጀርመኑ የአፍሪካ ሸላሚ ድርጅት ለዘንድሮው 2020 ሽልማት ኢልዋድን  የመረጠው ከ32 መሰሎቿ ጋር አወዳድሮ ነው።

ኢልዋድ  ሽልማቱን አስመልክታ እንደተናገረችው  “ሽልማቱ  ለቡድናችን  ታላቅ ማበረታቻና በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ጀርመን ለብዙ መርሀ-ግብራችን አስተማማኝና ዘላቂ ደጋፊያችን ናትና።” ብላለች።

የኢልዋድ ዓላማ፣ ጥረት፣ ተግባርና ውጤቷ ግን  ለብዙዎች አብነት መሆኑም ተገልጿል።

ሽልማቱን በሚቀጥለው ሣምንት በርሊን ውስጥ በሚዘጋጅ ሥነ ሥርዓት ትቀበላለች ተበሎ ይጠበቃል።

ሶማሊያን ያወደመው ጦርነት ሲባባስ የሁለት ዓመት ሕፃን የነበረችው ኢልዋድ  ከእናትዋ ጋር ወደ ካናዳ እንደተሰደደች ተገልጿል።

የኤሌክትሪክ ኢንጂነር አባቷ ኢልማን ዓሊ ግን በጦርነቱ የሚሳተፉ ወጣት  ተዋጊዎችን ከኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለመርዳት ሶማሊያ ቀርተው እ.አ.አ  በ1996 በታጣቂዎች ተገደሉ።

ኢልዋድ  አባትዋ በተገደሉ በ14ኛው ዓመት የአባትዋን ጅምር ከዳር ለማድረስ  እናትዋን አስከትላ ወደ ሶማሊያ ተመለሰኝ።

በአባቷ ሥም “የኤልማን የሠላም ማዕከል” ያለችዉን ድርጅት መሥርታ አባቷ የጀመሩትን ሥራ ቀጥሎ፣ የልጅ ወታደሮች እያስተማረ፣ በተለያየ ሙያ እያሰለጠነ፣ የሥነ ልቡና ድጋፍም እያደረገ ከኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እየረዳ መሆኑ ታውቋል።

ኢልዋድ ብዙ ፈተናዎችን ያለፈችና ከጥቂት ወራት በፊት ሞቋዲሾ  ውስጥ  እህቷ በጥይት ተመታ ተገድላባታለች።

ኢልዋድ ግን “አልማአስ (እህቷ)ን የምናስባት ለሰላም፣ለዕርቅ ለእኩልነት የምናደርገውን ትግል ስንቀጥል ብቻ ነው” ብላለች።

የኢልዋድ ድርጅት በአሁኑ ወቅት 172 ሠራተኞች ሲኖሩት በስምንት  ግዛቶች  ጽሕፈት ቤቶች መክፈቱን የዶቸ ቨለ ዘገባ አመልክቷል።

የወጣቷ ተግባር ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ እስከ ማሊና በመላው የቻድ ሐይቅ አዋሳኝ ሀገራት አብነት መሆኑንም ዘገባው አስረድቷል።

ኢልዋልድ እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት “የሠላም ግንባታ ድርጅት” ወጣት አማካሪም መሆኗም ታውቋል።

ባለፈው ሣምንት ኢልዋልድ ከወላጅ እናቷ ጋር በአርሜኒያ የዘር  ማጥፋት  ሰለባዎች ሥም የተሰጠውን የንቁ የሰው ልጅ የአውሮራ የ2020 ሽልማት ተሸላሚዎች መሆናቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም