ከሐምሌ 17 ጀምሮ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቅርጫት ኳስ የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና በሀዋሳ ይሰጣል

95
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2010 ዓለም አቀፍ የቅርጫት ኳስ የአንደኛ ደረጃ ስልጠና ከሐምሌ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሃዋሳ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን፣ የስፔኑ አሴዴ የትምህርትና ሳይንስ ድርጅትና የባርሴሎናው ጋቫ ካታላን የቅርጫት ኳስ ቡድን ስልጠናውን በጋራ አዘጋጅተውታል። እስከ ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆየው ይህ ስልጠና በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጸው በስልጠናው ላይ ከ50 እስከ 60 የአካል ብቃት መምህራን እንዲሳተፉ ታቅዷል። ከስፔን የሚመጡት ሰባት አሰልጣኞች ለመምህራኑ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንደሚሰጡም ተናግረዋል። አሰልጣኞቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቅርጫት ኳስ አሰልጣኝነት የደረሰበትን ደረጃና መሰረታዊ የአሰልጣኝነት መርሆዎችና ቴክኒኮችን በተመለከተ ለሰልጣኞቹ ግንዛቤ እንደሚያስጨብጡም አመልክተዋል። ስልጠናው በኢትዮጵያ ያለውን የቅርጫት ኳስ የአሰለጣጠን ደረጃ ለማሻሻልና ሌሎች አገራት በስፖርቱ የደረሰቡትን ደረጃ አውቆ ልምድ ለመቅሰም ያግዛል ብለዋል። ሰልጣኞች በስልጠናው መጨረሻ የሚሰጠውን ፈተና ካለፉ የዓለም አቀፍ የቅርጫት ኳስ የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል። ከስልጠናው በተጨማሪ ከስፔን የሚመጡት አሰልጣኞች በሀዋሳ በሚገኙ የቅርጫት ኳስ የታዳጊ ፕሮጀክቶች የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው አቶ ይመር ያስረዱት። በተጨማሪም ከስፔን የመጡት አሰልጣኞች ከሐምሌ 23 እስከ 26 ቀን 2010 ዓ.ም በወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የሙያ ማሻሻያ የአሰልጣኝነት ስልጠና እንደሚሰጡም አክለዋል። ስልጠናው በሁለቱም ጾታዎች ለኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሚገኙ ክለቦች አሰልጣኞች፣ ለዩኒቨርሲቲዎች የቅርጫት ኳስ ቡድንና ለክልል ቅርጫት ኳስ ቡድኖች አሰልጣኞች የሚሰጥ ነው ብለዋል። በአጠቃላይ በስልጠናው 40 አሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ገልጸው አሰልጣኞቹ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን የመውሰድ ተሞክሮ እንዳላቸው አብራርተዋል። እነዚሁ አሰልጣኞች በወልቂጤ ለሚገኙ የተዳጊ ቅርጫት ኳስ ፕሮጀክት ውስጥ ለሚገኙ 80 ታዳጊዎች የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው አቶ ይመር የተናገሩት። በቀጣይ ዓመት ከስፔኑ ሪያል ማድሪድ የቅርጫት ኳስ ቡድን ጋር በመተባበር መሰል ዓለም አቀፍ የአሰልጣኝነት ስልጠና ለመስጠት ጥረት መጀመሩን አስረድተዋል። በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎች በኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ስፖርትን ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጥረት አካል እንደሆነም አመልክተዋል። መረጃዎች  እንደሚያመላክቱት  ኢትዮጵያና የቅርጫት ኳስ ትውውቅ በ1930ዎቹ ላይ ይጀምራል። ዳግማዊ ሚኒሊክ፤ ተፈሪ መኮንን፤ ኮከበ ፅባህና ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ስፖርቱ በኢትዮጵያ አሀዱ ያለባቸው ናቸው። ቅርጫት ኳስ በአገራችን አንጋፋ ከመሆኑ ባሻገር በ1970ዎቹ እጅግ ተወዳጅና በተለይም በወጣቱ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘና ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገበት ቢሆንም  ከጊዜ በኋላ ግን እየተዳከመ  መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በ1948 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ በየደረጃው እየተስፋፋና ተወዳጅነት እያገኘ በመምጣቱ በሀገር ደረጃ የብሔራዊ ቡድን በማቋቋምና በ1954 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በመሳተፍ  አህጉር አቀፉን የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ተቀላቅሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም