የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የኢትዮጵያ ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምስጋና አቀረበ

108
አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2010 የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሁሉም የጸጥታ ዘርፍ አካላትና ወጣቶች ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ተናገሩ። ኮሚሽነር ጄኔራሉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሶስት ቀናት ይፋዊ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው መመለሳቸውን አስመልከተው መግለጫ ሰጥተዋል። በፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ወቅት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የጸጥታ አካላት በተለይም የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት እንዲሁም የአዲስ አበባና የደቡብ ፖሊሶችን አመስግነዋል። በመሆኑም ሂደቱ ስኬታማ በመሆኑ ''ውጤቱ የእናንተ ነውና እንኳን ደስ አላችሁ'' ብለዋል ኮሚሽነር ጄኔራሉ። ከዚህ ጎን ለጎን "የአዲስ አበባ ሕዝብ ሊመሰገን ይገባል" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በተለይም የአዲስ አበባ፣ የሀዋሳና የምዕራብ አርሲ ወጣቶች ያለምንም ክፍያ ሰላም ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ነው ያሉት። ኮሚሽነር ጄኔራሉ የሀዋሳና የምዕራብ አርሲ ወጣቶች ተራ በተራ ጫካ ውስጥ እያደሩ ሰላም ሲያስከበሩ አንደነበረ አንስተው፤ ለዚህ ላማረ ስራቸውም ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። ሕዝቡም ሆነ ወጣቶች ተግባራቸው ስኬታማ በመሆኑና በዚህ ታሪካዊ ተግባር ተሳታፊ በመሆናቸውም ሊኮሩ ይገባል ብለዋል። በቀጣይም የፀጥታ አካላት የሚቆሙት ለሁሉም ሕዝብ ሰላም በመሆኑ ሁሉም ሕብረተሰብ ይህንን በመረዳት ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን ሰላምና ፀጥታን ማስጠበቅ ይኖርበታል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም