ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ገብቶ ዜጎችን እንዲጠብቅ አዘዙ

315
አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ገብቶ የዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቅ ትዕዛዝ አስተላለፉ። ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ከሁለቱም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች በክልሎቹ አጎራባች አካባቢዎች የፌደራል የጸጥታ አካላት በአፋጣኝ ገብተው የሰላምና መረጋጋት ሥራ እንዲሰሩ ተስማምተዋል። የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚታየው የዜጎች ሕይወት መጥፋት እንዲያቆም፣ ግጭቶችን የሚያባብሱ አካላትን ለማስቆምና ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለመከላከል ሕግ የማስከበር ሥራቸውን እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የሰጡትን መመሪያ ተከትሎም የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸውም ግጭት በተፈጠረባቸው አጎራባች አካባቢዎች የፌደራል የጸጥታ ኃይል በመግባት የጸጥታ፣ የሠላምና  መረጋጋት ሥራ እንዲሰራ፤ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተስማምተዋል። ለአፈጻጸሙ የሁለቱም ክልል መንግሥታት ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚወጡ ርዕሳና መስተዳደሮቹ ማረጋገጣቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒሰትር አቶ አህመድ ሺዴ ገልጸዋል። በተለይ የሕግ-ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራና የሁለቱም ክልል ሕዝብ እንደወትሮው የለውጥ ሂደቱን በመጠበቅ ለመፍትሄው ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። በቀጣይ በበርካታ እሴቶች የተሳሰረውን የሁለቱ ክልል ሕዝብ ከመሰል ግጭቶች በመከላከል  ለዘላቂ መፍትሄ፣ ለሰላምና ፍቅር አብሮ የሚሰራበትን ሁኔታ ለማስቀጠል ተከታታይ የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፍረንሶችን በአፋጣኝ ለማካሄድም ርዕሰ መስተዳደሮቹ ወስነዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም