ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሰላም ጉዞ እንቅፋት የሚሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰቡ

4228

አዲስ አበባ ሃምሌ 9/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የሰላም ጉዞ ላይ እንቅፋት የሚሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መከላከያ ሰራዊትና ፌዴራል ፖሊስ በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቆም በሕጋዊ መንገድ ጣልቃ እንድትገቡ ብለዋል።

ዶክተር አብይ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት እየተከሰተ፤ ዜጎች ለአደጋ እየተዳረጉ ነው፤ በተለይም ችግሩ በሶማሌ ክልል የከፋ በመሆኑ የሰው ህይወት እየጠፋ ይገኛል ነው ያሉት።

በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ብቻ ሳይሆን በደቡብና በሰሜን ኢትዮጵያ “ግጭት የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች አሁን ለምናስበው ፍልስፍና ጠቃሚ አይደሉም” ብለዋል።

“ዜጎች ወደ ግጭት እንዲገቡና ወዳልተፈለገ ነገር እንዲያመሩ በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን ራቅ ብለው ክብሪት የሚያቀብሉ፤ ነዳጅ የሚያቀብሉትንም ይመለከታል” ነው ያሉት።

“በሰዎች መጋጨትና በሚፈጠረው ቀውስ ውስጥ ማደግ ያለ የሚመስላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ” ሲሉም አሳስበዋል።

”ህዝብ ጫንቃ ላይ ተጭነን ለመንገስ የምናደርጋቸው ትግሎች ሄደው ሄደው በታሪክ ፊት ተወቃሽ ያደርገናል” በማለትም ነው የተናገሩት።

አክቲቪስቶች፣ አርቲስቶች፣ በተለያየ ሙያ ያሉ ሰዎች፣ ቆስቋሽና የሚያጋጩ ጉዳዮችን ከማድረግ ይልቅ፤ የሚያስማሙ፣ የሚያስታርቁ፣ የሚያቀራርቡ ስራዎችን በመስራት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ መክረዋል።

“ድሃው እኛን አምኖ ህይወቱን እየገበረ ስለሆነ ድርጊቱ እንዳይሰፋ፤ ሰዎች እንዳይሞቱ፣ ንብረት እንዳይወድም፤ እውቀት ያለው ጥበብ ያለው ተባብሮ ሰላም ለማስፈን ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።

ስለሆነም ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ የአገር መከላከያ ሰራዊትና ፌዴራል ፖሊስ በግጭቶች መሀል እየገቡ ሙያዊ ጥበብ በታከለበት መንገድ አገራዊና ሕገ-መንግስታዊ ግዴታቸውን በመወጣት ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።