በአዲስ አበባ በዓለም አቀፍ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ 14 የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በዓለም አቀፍ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ 14 የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር አባላት ትናንት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ባደረጉት ፍተሻ 13 ናይጄሪያውያንና አንዲት ብራዚላዊትን በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ሰዎቹ  የተያዙት በላቲን አሜሪካ አካባቢ የሚመረትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘዋወር ከ14 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮኬይን የተሰኘ አደገኛ ዕፅ ይዘው መገኘታቸውን የዘርፉ የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መንግሥትአብ በየነ ገልጸዋል።

መነሻቸውን የብራዚሏ ሳኦፖሎ ከተማ መዳረሻቸውን ደግሞ የተለያዩ አገሮች አድርገው ሲጓዙ እንደነበሩ ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ሰዎቹ ዕፁን በውስጣዊና ውጫዊ የሻንጣ አካል በመደበቅ፣በሆዳቸው በመዋጥ እንዲሁም የጡት ማስያዣና የተለያዩ የማዘዋወሪያ ዘዴዎችን ተጠቅመው ለማሳለፍ መሞከራቸውን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዘርፉ ባለፉት ሶስት ወራት በአደገኛ ዕፅ ዝውውር ወንጀሉ ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 24 ሰዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ 39 ኪሎ ግራም ኮኬይንና 36 ኪሎ ግራም የሚመዝን ካናቢስ የተባለ ዕፅ መያዙን ተናግረዋል።


ህብረተሰቡ የጸጥታ አካላት የአደገኛ ዕፅ ዝውውር ለመከላከል ትብብር እንዲያደርግ የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም