በጋምቤላ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የህዝብ ንቅናቄ መፍጠሪያ መረሃ ግብር ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የህዝብ ንቅናቄ መፍጠሪያ መረሃ ግብር ተጀመረ

ጋምቤላ፣ ጥቅምት 07/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የህዝብ ንቅናቄ መፍጠሪያ መረሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀመረ።
በመረሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ አኳይ አቡቲ እንዳሉት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ቀዳሚ የጤና ችግር የሆነውን የወባ በሽታ ነው።
በሽታው ችግር የሚያደረሰው በተለይም በክረምቱ መግቢያና መውጫ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በግብርና ልማት ስራው ላይ ሳይቀር ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ የወባ መራቢያ አካባቢዎችን በማጽዳት፣ አጎበርንና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም በሽታውን መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሩት ጋትዊች በበኩላቸው ከጤና ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የክረምት መግቢያና መውጫ ወቅቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ቢሮው በ111 ሺህ 250 ቤቶች ላይ የፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ማካሄዱን ጠቅሰው ለ115 ሺህ 416 አባወራዎች ደግሞ የአልጋ አጎበር ማሰራጨታቸውን አሰታውቀዋል።
በክልሉ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም በተፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ለዚህም ማሳያው በ2007/ 2008 በክልሉ አጠቃላይ ምርመራ ካደረጉ ሰዎች መካከል 98 ሺህ 111 በ2011/2012 ደግሞ 68 ሺህ 773 ሰዎች በበሽታው ተይዘው መገኘታቸው ነው ብለዋል።
በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተመልክቷል።
የተጀመረው ንቅናቄ መረሃ ግብር የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በሽታውን ለመከላከል መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ በረሄ ከላይ ናቸው።
"ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል “ በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው የንቅናቄ መረሃ ግብር ከክልል እስከ ቀበሌ አካባቢን በማጽዳትና የህዝቡን ግንዛቤን በሚያሳደግ መልኩ ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይም አስተባባሪው ገልጸዋል።
በዕለቱ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን የማጽዳት መረሃ ግብር ተካሂዷል።