የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የምግብ እጥረትን እያባባሰ መሆኑን ፋኦ አስታወቀ

99

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የምግብ እጥረትን እያባባሰ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) አስታወቀ።

የፋኦ ረዳት ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ ተወካይ አበበ ኃይለገብርኤል ለዢንዋ እንዳሉት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ችግርን እያባበሰ ይገኛል።

በአፍሪካ ወረርሽኑ ከመከሰቱ በፊት ከ256 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበር አስታውሰው ከወረርሽኙ በኋላም ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል።

የብዙዎች ትኩረት የነበረው ወረርሽኙ የህብረተሰብ ጤና ላይ ችግር ያስከትላል የሚል እንጂ የምግብ ዋስትና ጉዳይ ያን ያክል ትኩረት እንዳልተሰጠው አብራርተዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ በአፍሪካ የምግብ እጥረት ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል ሲሉ ለዥንዋ ገልጸዋል።

የወረርሽኙ ሁኔታ እየተባባሰ ከመጣ ከጤና ስጋትነቱ በተጨማሪ የምግብ ዋስትና ላይም ስጋት መደቀኑ አይቀርም ነው ያሉት።

ችግሩን ለመፍታት ብዙ ምርት ካለባቸው አካባቢዎች በማጓጓዝ እጠረት ወዳለባቸው ማድረስ ያስፈልጋል ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ዓለማችን አሁን ላይ በቂ ምርት ቢኖራትም ፍትሃዊ ስርጭት ግን የለም።

በተለያዩ አገራት ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች የምግብ እጥረት እየገጠማቸው ይገኛል።

በኮቪድ 19 ምክንያት ስራ ያጡ በርካታ አፈሪካዊያንም ይበልጥ ለችግር እየተዳረጉ ይገኛሉ።

ይህም የሆነው በዓለም ላይ የምርት እጥረት አጋጥሞ ሳይሆን የአቅርቦትና ስርጭት መጓደል መሆኑን የአፍሪካው ተወካይ ጠቅሰዋል።

በአውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1945 በኢጣሊያ ሮም የተመሰረተው ዓለም አቀፉ የምግብና የእርሻ ድርጅት 75ኛ ዓመቱን በትናንትናው እለት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም