ሀገር አቀፍ የካዳስተር መተግበሪያ ሶፍትዌር ይፋ ሆነ

149

ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) ህጋዊ የካዳስተር ስርዓትን ቀልጣፋና ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር የሚያስችል የመተግበሪያ ሶፍትዌር በአዳማ እየተካሄደ ባለው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሴክተር ጉባኤ ላይ ተመርቋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተሰራው ይኸው ሶፍትዌር የዜጎች የይዞታ መብት እንዲረጋገጥና በዘርፉ የሚታየውን ውስብስብ የሆነ አሰራር ግልፅ ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተነግሯል።

የመተግበሪያ ሶፍትዌሩን የመረቁት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የስራ ሀላፊ የሆኑ ሴት ሚኒስትሮች የመተግበሪያው እውን መሆን ከመሬትና ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ለሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችና እንግልቶችንም ለማስቀረት የሚያስችል በመሆኑ በፍጥነት ወደተግባር መግባት ይኖርበታል ሲሉ ገልፀዋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጎ ተስፋዬ የመሬት ምዝገባ ጉዳይ ህብረተሰቡን ያማረረ ለኪራይ ሰብሳቢነት ያጋለጠና ስንቸገርበት የቆየ ጉዳይ በመሆኑ ይህንን ሊፈታ የሚችል ሶፍትዌር ተሰርቶ ይፋ መደረጉ ትልቅ እፎይታ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሰኒ በበኩላቸው ጉዳዩ ውስብስብና ብዙ ጊዜ ህብረተሰቡና መንግስትም ጭምር ሲቸገርበት የቆየ፣ አሰልቺ የሆነ ቢሮክራሲ ያለበት፣ ሀብትንም ያባከነና በተጨባጭ ለውጥ ያልመጣበት እንደነበር ገልፀው፤ የመተግበሪያው እውን መሆን እጅግ አስፈላጊና በፍጥነት በተግባር ላይ መዋል ይኖርበታል ብለዋል።

የክልሉ መንግስትም መተግበሪያውን ወደመሬት ለማውረድና ለመተግበር ዝግጁ ነው ሲሉ ተናግረዋል።የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋም መተግበሪያው ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መሬትን እንደ ትልቅ ሀብት እንዲታይ የሚያደርግ ፣ተገማች አሰራርን የሚዘረጋና ህጋዊ ማረጋገጫ መስጠት የሚያስችል በመሆኑ በፍጥነት ወደተግባር ገብቶ ለማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው አሰራሩን ከተሞች ለማስጀመር ዝግጅት እንዲያደርጉና በፍጥነትም ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡ ስለአሰራሩ ማወቅ እንዲጀምርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም