የህወኃት አመራሮች እየፈጸሙት ያለው ህገ-ወጥነት ከፖለቲካ ልምዳቸው አኳያ ተገቢ አለመሆኑን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ

716

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2013(ኢዜአ) የህወኃት አመራሮች እየፈጸሙት ያለው ህገ-ወጥ ድርጊት ካላቸውን ረጅም የፖለቲካ ልምድ አኳያ ተገቢ አለመሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ለትግራይ ህዝብ ክብርና ጥቅም ሲባል የፌዴራል መንግስትና የህወኃት አመራሮች በድርድር ችግራቸውን ሊፈቱ ይገባልም ነው ያሉት።

በኢፌዴሪ ህገ- መንግስት አንቀፅ 102 ንኡስ ቁጥር 1 መሰረት በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የማስፈፀም ስልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል።

በኢትዮጵያ ወረርሽኙ መከሰቱ እንደታወቀ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚመለከታቸው ባለደርሻ አካላት ጋር በመካከር ቦርዱ ቀደም ሲል ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ የማይችል መሆኑን አሳውቋል።

ይሁንና በትግራይ ክልል ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጭ ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም ክልላዊ ምርጫ ተካሂዷል።

ምርጫው የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ያለው የህወኃት አመራሮች ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል።

የህወኃት አመራሮች እየፈጸሙት ያለው ህገ-ወጥ ድርጊት ካላቸው የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ልምድ አኳያ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፤ ህወኃት እራሱ መራጭ፣ አስመራጭ፣ ታዛቢ አጠቃላይ ሁሉን ነገር ሆኖ አካሄድኩት ያለው ምርጫ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።


የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጊደና መድህንም በምርጫ ዙሪያ ህወኃት ያደረገው ድርጊት ከፓርቲው የማይጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል። 

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሰብሳቢና የምርጫ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ የሱፍ ኢብራሂም ደግሞ ህወኃት በፊትም ህገ መንግስት አክበሮ አያውቅም፤ አሁንም ያከብራል ተብሎ አይጠበቅም ብለዋል።
ጥቂት የህወኃት ቡድኖች እየፈጸሙት ያለውን ህገ-ወጥ ድርጊት የፌዴራሉ መንግስት በሆደ-ሰፊነት ማለፉ ለትግራይ ህዝብ ያለውን አክብሮት ማሳያ መሆኑን የፓርቲዎቹ አመራሮች ገልጸዋል።

በመሆኑም ህወኃት ለራሱ ጥቅም ብቻ ከመቆም ወጥቶ ለትግራይ ህዝብ በማሰብ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር በመወያየት መፍትሄ መፈለግ አንዳለበትም ፓርቲዎቹ አመራሮች አሳስበዋል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሰብሳቢና የምርጫ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ የሱፍ ኢብራሂም እንደሚሉት በአገሪቷ ለበርካታ ዜጎች ህይወትና ንብረት መጥፋት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የህወኃት እጅ ያለበት በመሆኑ ድርጅቱ በህግ መጠየቅ ይኖርበታል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ የትግራይ ክልል ያካሄደው ምርጫ ተቀባይነት የሌለውና ዋጋ ቢስ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ከተመሰረቱ የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ አካል ጋር የፌዴራል መንግስት ምንም አይነት ግንኙነት እንደማያደርግ ወስኗል፡፡

በሌላ መልኩ የፌደራል መንግስት የትግራይን ህዝብ የልማትና መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎት ማዕከል በማድረግ የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደርን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ህጋዊ ተቋማት ብቻ የስራ ግንኙነት የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቋል።

የተወሰኑ ሕገ ወጥ አካላት በሚፈጽሙት ድርጊት የክልሉ ህዝብ መጎዳት ስለሌለበት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቀጣይነት ያለው ጥረት ይደረጋልም ተብሏል።