"ለአፍሪካ ከእስካሁኑ የተለየ፣ ተሻጋሪ፣ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ያስፈልጋታል"-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

135

አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2013 (ኢዜአ) "ለአፍሪካ ከእስካሁኑ የተለየ፣ ተሻጋሪ፣ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ያስፈልጋታል" ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

የአህጉሪቱ የመረጃ ሥርዓት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ''ከፍተኛ'' ተጽዕኖ አሳድሮበታል ተብሏል፡፡

ሰባተኛው የአፍሪካ የስታቲስቲክስ ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አማካኝነት ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በቨርቹዋል ውይይት መከበር ተጀምሯል፡፡

ውይይቱም "የአሥርት ዓመታቱን የአፍሪካ ብሔራዊ የስታቲስቲካል ሥርዓት ከዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ተጽዕኖ ለማውጣት የሚያስችል ቀጠናዊ መፍትሄ ማበጀት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ውይይቱን በይፋ ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት አህጉሪቱ የመረጃ ሥርዓቷን የምታዘምንበት አሰራር መዘርጋት ይጠበቅባታል፡፡

አህጉሪቱ የያዘቻቸውን ዘላቂ የልማት አጀንዳና የአፍሪካ ህብረትን ብሔራዊ የልማት ዕቅድ ለማሳካት ጥራት ያለው መረጃ ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ የመረጃ ሥርዓት በኮቪድ-19  ወረርሽኝ ምክንያት ''ከፍተኛ'' ተዕእኖ እንዳሳደረበት ያመለከቱት ፕሬዚዳንቷ፣ ወረርሽኙ ካሳደረበት ችግር ለማውጣት አገሮች በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡  

"በአህጉሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመርጃ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግም መረጃን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ በመቅረጽ ምርትን ለማሳደግ፣ የህዝብን ፍላጎት ለማሟላትና ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይረዳል" ብለዋል፡፡

የአፍሪካውያንን ጾታዊ እኩልነት ለማረጋገጥም ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ወደፊት የሚደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሂደት በኮቪድ-19 ተጽዕኖ ያረፈበትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል  አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም ብሔራዊ የመረጃ ሥርዓቱን በማዘመን በእውነት ላይ የተመሰረተ ወቅታዊ፣ ተዓማኒና ዘላቂ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ለመፍጠር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት አበራሽ ታሪኩ በበኩላቸው "ውይይቱ በኮቪድ-19  ምክንያት ተጽእኖ ያረፈበትን የመረጃ ሥርዓት የሚያሻሽሉ አመላካች ጉዳዮችን ለማንሳት ይጠቅማል" ብለዋል፡፡

"በኮቪድ-19  ምክንያት በአህጉሪቱ የደረሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመዳሰስ ምላሽ የሚሰጥባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል" በማለትም ከውይይቱ የሚጠበቀውን ውጤት ጠቁመዋል፡፡

ይህም በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ በኮቪድ-19  ምክንያት የደረሱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን በመለየት የማስተካከያና የድጋፍ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚረዳ አንስተዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንጌ የአህጉሪቱን ልማት ለማፋጠን ጥራት ያለው፣ ዘመናዊና ተደራሽ የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር ያሻል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የዲጂታል ስታቲስቲካል ሥርዓትን መጠቀምና ማጠናከር፣ አገሮችና አለም ዓቀፍ ተቋማት በትብብር መሥራት እንደሚኖርባቸው  አሳስበዋል፡፡

ኮቪድ-19 ባስከተለው ተጽዕኖ ሳቢያ በርካታ የአፍሪካ አገሮች  የሕዝብና ቤት ቆጠራ አለማድረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡

በቀጣይ የሚካሄዱ የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙና ጥራት ያላቸው ለማድረግ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት መዘርጋት  እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ይህም በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ከኮቪድ-19  ውጭ ያሉ በሸታዎች ለመለየትና በአፋጣኝ ለመቆጣጠር፣ ፆታዊ እኩልነት ለማረጋገጥ፣ ለፖሊሲ ዝግጅትና ዕቅድ ቀረጻና ማስፈጸም ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በውይይቱም አፍሪካ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ሥርዓትን በመዘርጋት የሕዝቦቿን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባት ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም