ኤጀንሲው የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን አስታወቀ

63

አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2013 (ኢዜአ) የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የአምስት ዓመታት የሳይበር ደህንነት ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ገለጸ።

ድርጅቱ የአዲስ የመለያ ዓርማም ይፋ አድርጓል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተቋሙ እንደ አገር የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂ ክለሣ አድርጓል።

በዚህም ዲጂታል ኢኮኖሚውን ከሳይበር ጥቃት ለመጠበቅ፤ የነገን ዲጂታል ኢኮኖሚ ሥነ ምህዳር ታሳቢ ያደረጉ፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ተዋናይ እንድትሆን ብሎም ጥቅሞቿን እንድታስከብር የለውጥ ሥራዎችን መቅረጹን አስታውቀዋል።

በስትራቴጂው በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ሌሎች የግል ተዋናዮችን ማሳተፍ እንዲሁም ከተቋሙ ተልዕኮ ውጭ የነበሩ ሥራዎችን ወደሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ማስተላለፉንም ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ዓመት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ መነሻቸውን ከአንድ አገር ያደረገ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገው ሙሉ በሙሉ መክሸፋቸውን አስታውሰዋል።

ወደፊትም ኢትዮጵያ በምትገነባቸው የመሠረተ ልማት ተቋማት ማስቆም የሚሳናቸው ኃይላት የሳይበር ጥቃት ውስጥ እንደሚገቡ ገልጸው፤ እነዚህንም ከጥቃት ለመጠበቅ ተቋሙ አቅሙን በማሳደግ ይጠናክራል ብለዋል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች እየጨመረ መምጣቱን በመግለጽም ከፋይናንስ፣ ከመገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያለችበትን የጂኦ ፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታና የዲጂታል ዓለም አሁናዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ዶክተር ሹመቴ አንስተዋል።

ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች በኢንተርኔት አጠቃቀምና ከሳይበር ጥቃት መጠንቀቅ እንዳለባቸው ገልጸው፤ ኢንሳ በ24 ሰዓት የሳይበር ደህንነት ጥበቃ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ለዚህ ተልዕኮው ይወክላል ያለውን የመለያ ወይም ሎጎ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የመለያ ዓርማውም ድርጅቱ ለሳይበር ደህንነት ጋሻነቱን ወካይ ትዕምርት እንደሆነ  ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዓርማው ቀይና ሰማያዊ ቀለማት ያሉት ሲሆን፤ ሰማያዊው የኤጀንሲውን ሰላማዊ የመከላከልና የጥበቃ ሥራዎችን፣ ቀዩ ደግሞ ጥቃት ከተሰነዘረበትም መለሶ ማጥቃት እንደሚችል፣ የንስር ዓይኑ በንቃትና በጥልቀት ተመልካችነቱ እንደሚወክል ተብራርቷል።

የቁልፍ ምልክቱም ሳይበር የተዘጉትን መክፈት፣ የተከፈቱትን የመዝጋት ተልዕኮዎች ሲወክል፣ ሌሎች ምልክቶች የቴክኖሎጂ ሥራዎችን ወካይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም