ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ትስስር ያጠናክራል ---አስተያየት ሰጪዎች

62
ጭሮ/ ነቀምቴ ሀምሌ 8/2010 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ  ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የተነፋፈቁ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በማገናኘት ትስስራቸውን እንደሚያጠናክር በጭሮ ከተማና ምስራቅ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ሁለቱ ሃገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመገናኘት በመብቃታቸው ከፍተኛ የደስታ ስሜት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ዶክተር  አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ ወዲህ  ለሰላም፣ ለይቅርታና ለፍቅር እንዲሁም ለመደመር በሳዩት እንቅስቃሴ ፈጣን ለውጥ ማምጣት ችለዋል፡፡ ከጭሮ ከተማ  የዜሮ አንድ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ሜሮን ለገሰ በሰጡት አስተያየት በተለይ የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ሲፈልጉትና ሲናፍቆት የቆዩ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ "ለዓመታት ተለያይተው የቆዩትን ወንድማማች ህዝቦች  ለማገናኘት በሁለቱም ሃገራት መሪዎች የተደረገው ጥረት ይደነቃል "ያሉት ወይዘሮ ሮማን ይህም ሰላምና አንድነት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል። "በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም ሰፍኖ የዛሬን ቀን ለማየት ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት ነበረኝ በተለይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ኢትዮጵያ በመምጣታቸው በጣም ደስተኛ ነኝ" ያሉት ደግሞ አቶ ደሳለኝ ሰብስቤ የተባሉት የከተማው ነዋሪ ናቸው። አሁን የተገኘው ሰላም የበለጠ ደምቆና አብቦ ከመሪዎቹ ባለፈ ለዘመናት ተለያይተው ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች  ለመገናኘት እንዲበቁና  ትስስራቸው እንዲጠናከር ፍላጎታቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ወጣት አስቻለው ኪዳነማርያም በበኩሉ " ሰላማዊ ግንኙነቱ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ ለሆኑት የሁለቱም ሀገራት ወጣቶች ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው" ብሏል፡፡ የተጀመረው ሰላም ተጠናክሮ ለውጡን ለማገዝ እንደሚደግፍም ተናግሯል። " ከኤርትራ ጋር  በፍቅር ስንሰለት ያስተሳሰሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ክብር ይገባቸዋል"  ያሉት ደግሞ በከተማዋ የቀበሌ ሶስት ነዋሪ  የ76 ዓመቱ አዛውንት አቶ ኃይሉ ወልደማርያም ናቸው፡፡ በዕድሜያቸው ሶስት መንግስታትን እንዳዩ ያመለከቱት አቶ ኃይሉ እንደዚህ በሰላምና በፍቅር ህዝብን ከህዝብ ለማስተሳሰር የሚሰራ መሪ እንዳለዩ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች ዶክተር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩትን ለውጥ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅና ያለፉት ችግሮች በቀጣይ እንዳይደገሙ በትኩረት በመስራት እንዲደግፉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በተመሳሳይ ከምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  አቶ አምደሚካኤል ጃለታ በሰጡት አስተያየት የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ታሪካዊ ከመሆኑም በላይ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ተናገረዋል፡፡ በደም ፣በባህል፣በሥነ ልቦና ፣በማህበራዊ ሕይወትና በሌላም የነበራቸው የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተለያይተው ቢቆዩም አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ መልካም ግንኙነታቸው እየተመለሰ ነው፡፡ በዚህም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አቶ አምደሚካኤል ገልጸዋል፡፡ የጊዳ አያና ወረዳ የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በየነ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ሻክሮ የነበረው ግንኙነት ለማስተካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉት ጥረት ውጤታማ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በነበረው ችግር ተለያይተው የቆዩት ህዝቦች አሁን መገናኘት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን  የገለጹት ደግሞ  የዲጋ ወረዳ የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሮማን አቢዩ ናቸው፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት  ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት መጠናከር እንደሚበጅ ጠቅሰው በግጭት ውስጥ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራትም መልካም ምሣሌ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ትስስርን በማጠናከር ለአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የተናገሩት ደግሞ የምሥራቅ ወለጋ ዞን የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በሪሶ ተመስጌን ናቸው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም