በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ቦረዳ ከተማ የሰው ህይወት ያጠፉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ቦረዳ ከተማ የሰው ህይወት ያጠፉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

ሀረር፣ ጥቅምት 3/2013 (ኢዜአ ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቦረዳ ከተማ በህግ ጥላ ስር የነበሩ ግለሰብ ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸሙ ሁለት ተከሳሾች በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ::
የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ አሸናፊ ሼዱ ለኢዜአ እንደገለጹት ቅጣቱ የተላለፈው በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱት መገርሳ ያሲን እና አረቢ ሻዶ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ነው።
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጃዋር መሃመድ ተከብቤያለሁ በሚል ካስተላለፈው ጥሪ ጋር ተያይዞ ሰልፍ በመውጣት በከተማው በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ላደረሱት የነፍስ ማጥፋት ወንጀልና ንብረት ማውደም ውሳኔው መተላለፉን ዳኛው ተናግረዋል።
ተከሳሾቹ ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር የነበሩ አንድ ግለሰብን በአስገዳጅ ሁኔታ በሃይል በመውሰድ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመግደላቸው በአቃቢ ህግ ማስረጃዎች መረጋገጡንም ዳኛው ተናግረዋል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የአቃቢ ህግ ምስክር ሊከላከሉ ባለመቻላቸውና ወንጀለኛነታቸውም በመረጋገጡ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ያስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ መሰል የወንጀል ድርጊቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ የሚያስተምርና ህዝቡንም የሚታደግ መሆኑንም ዳኛው አቶ አሸናፊ ሼዱ አስረድተዋል።