የኤርትራው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በጋራ የመልማት ፍላጎት ማሳያ ነው---የአማራ ክልል የምክር ቤት አባላት

64
ባህርዳር ሀምሌ 7/2010 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በደም የተሳሰሩት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በጋራ የመልማት ፍላጎት  ማሳያ መሆኑን የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል  አቶ ወርቁ ኃይለማሪያም እንደገለጹት የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ህዝቦች  ተቆራርጠው መኖር እንደማይችሉ ከመሪዎች አቀባበል መረዳት ይቻላል። ቀደም ሲል በመሪዎች ደረጃ ተቀራርቦ ለመወያየት ፍላጎቱ ባለመኖሩ በደምና በአጥንት የተሳሰረ ህዝብ እንደ ጠላት እንዲተያይ ሆኖ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት የሰላም ጥሪ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ  አፈወርቂ ጊዜ ሳይሰጡ የህዝቦችን አንድነት ተረድተው መምጣታቸው  በጋራ  አብሮ የመልማት ፍላጎት ማሳያ መሆኑን  አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡ "የፍቅርን አያልነት  ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመማር የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች አሁን እያሳዩት ያለውን መነፋፈቅና አንድነት አጥብቀው ሊይዙት ይገባል" ብለዋል። አንድ የነበሩት ህዝቦች ላለፉት 20 ዓመታት  ተለያይቶ ለመኖር የተገደዱት የህዝቡን ፍላጎት መሰረት አድርገው መሪዎች ሊሰሩ ባለመቻላቸው እንደሆነ የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል ሀጂ ዓሊ ሸፉ ናቸው። "  የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች የመሪዎች አቀባበል የሚያሳየው መሪዎች ከጀመሩልን እኛ እንጨርሰዋለን የሚል ነው " ገልጸዋል። ሌላው የክር ቤት አባል አቶ ብሩ ይማም በበኩላቸው አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተደረገ ያለው የአንድነት መንፈስ ከአፍሪካ አልፎ ዓለም ሊማርበት የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "ለ20 ዓመታት ተነጣጥለው የነበሩትን ህዝቦች አንድ ለማድረግ በሳልና ፍቅርን ከህዝባዊነት ጋር አጣምሮ የያዘ መሪ ይፈልግ ነበር፤ ጊዜው ሲደርስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እውን ሆኗል" ብለዋል አቶ ብሩ ። ከዚህ በኋላ ህዝቡ ኃላፊነቱን ተቀብሎ ከመሪዎች ጎን በመቆም  የነበረውን አንድነትና መተሳሰብ ሊያስቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ  የፕሬዝዳንቱ መምጣት በደም የተሳሰሩት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አብሮነትና በጋራ የመልማት ፍላጎት  ማሳያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም