ብልፅግና ፓርቲ የሀገሪቱን ሁለትናዊ እድገት እውን ለማድረግ እየሰራ ነው --የፓርቲው አባላት

ሐረር መስከረም 27 ቀን 2013 (ኢዜአ)-ብልፅግና ፓርቲ እውነተኛ ፌደራሊዝም በማረጋገጥ የሀገሪቱን ሁለተናዊ እድገት እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በሀረሪ ክልል በስልጠና ላይ ያሉ የፓርቲው አባላት አስታወቁ። 

የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ በክልሉ በወረዳና ቀበሌ ደረጃ ለሚገኙ አባላት የአቅም ለግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ከሰልጣኞች መካከል አቶ ቢኒያም ፀጋዬ እንደገለጹት  ፓርቲው እውነተኛ ፊዴራሊዝምን ለመገንባት እየሰራ ነው።

እየተሰጠ ባለው ስልጠና የህዝብ ጥያቄን በማዳመጥ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን አቅም ማዳበራቸውን ተናግረዋል ።

ወይዘሮ አየለች አሰፋ በበኩላቸው ፓርቲው ዘመን ተሸጋሪና ለትውልድ የሚተላለፍ ራዕይና አላማ ያለው መሆኑን ተናግረዋል ።

"ከከፋፋይና ፈራጅ የፖለቲካ አመለካከት ወጥቶ ዜጎችን በወንድማማችነትና በአንድነት የሚገነባ እውነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝምን ለማረጋገጥ እየሰራ ያለ ፓርቲ ነው" ብለዋል ።

ከስልጠናው ባገኙት ግንዛቤ በመታገዝ ህብረተሰቡ ለረጅም አመት ሲጠይቅ የነበረውን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰሩ አመላክተዋል ።

የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ እንደሚተጉም ገልጸዋል ።

"በስልጠናው ከአካባቢያዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ግልፅና ነፃ የሆነ ውይይት አድርገናል" ያሉት ደግሞ አቶ ታጁ ኡስማኤል ናቸው።

ስልጠናው በፈፃሚው በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል ።

አቶ ኤልያስ አሸናፊ በበኩላቸው "ስልጠናው ቀደም ሲል የነበሩ ብዥታዎችን ከማጥራት አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው" ብለዋል።

"በቀጣይ ማህበረሰቡን በቅንነት ለማገልገልና የሚነሱ አሉባልታዎችን ለማጥራት ተዘጋጅቻለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም