ፋውንዴሽኑ በወላይታ ዞን ለሚያስገነባው የሕዝብ ቤተ መጻህፍት ከጃፓን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ አገኘ

245

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26/2013 (ኢዜአ) የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በወላይታ ዞን ለሚያስገነባው የሕዝብ ቤተ መጻህፍት ከጃፓን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ተደረገለት።

ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት፣ ድጋፍ የሚሹ እናቶችና ህፃናትን ለመርዳትና በሥራ ፈጠራ ላይ ለመሰማራት ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል።

የጃፓን መንግሥትም ፋውንዴሽኑ በወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ጋቸኖ ቀበሌ ለሚያስገነባው  የሕዝብ ቤተ መጻህፍት የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ማትሱናጋ ዳሱኬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ1989 ወዲህ በኢትዮጵያ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች በአገራቸው ድጋፍ ተገንብተዋል።

መንግሥታቸው ማህበረተሰብ ተኮር በሆኑ በትምህርት፣ የሙያ ስልጠና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በጤናና ምግብ ዋስትና ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለፋውንዴሽኑ የተደረገው የገንዘብ ድጋፍም ጃፓን ኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዕውቀትን በማስፋፋት በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ ብሩህ ተስፋ ይፈጥራል ብለዋል።

የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ሥራአስፈጻሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት  እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

በዚህም የጃፓን መንግሥት የፋውንዴሽኑ ዓላማ ተረድቶ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ከጃፓን መንግሥት ጋር የሚኖረው ግንኙነት የመጀመሪያው እንጂ፤ የመጨረሻው እንደማይሆን ገልጸው፣ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም አረጋግጠዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የፋውንዴሽኑ መስራች አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፋውንዴሽኑ በአፋር፣ በደቡብ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስባቸው ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽን በሥራቸው ላይ እንቅፋት ቢፈጥርም፤ የሰው ኃይል ከማሟላትና ችግሮችን ከመለየት ባለፈ ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ የሚሆን ድጋፍ ሲያሰባስብ መቆየቱን አስረድተዋል

በኢትዮጵያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ እናቶችና ህጻናትን ለመደገፍ፣ በተፈጥሮ ሃብቶች ቱሪዝምን ለማሳደግና በወጣቶች ፈጠራ ላይ ያተኩረው ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከተቋቋመ አንድ ዓመት አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም