በምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ የሆኑ 2 ሺህ 241 ዜጎች ወደ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ተሸጋገሩ

68

መስከረም 26/2013 (ኢዜአ) በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በመጀመሪያው ዙር የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ የሆኑ 2ሺህ 241 አባውራና እማውራዎች ተመርቀው ወደ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ተሸጋገሩ፡፡

አባውራና እማውራዎቹ ከ8 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ያሏቸው ሲሆን በቀጣይ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ የሥራ ዘርፍ ይሰማራሉ ተብሏል፡፡

በኢንተርፕራይዝ ዘርፉ ሲሰማሩም የገንዘብ ችግር እንዳያጋጥማቸው ለእያንዳንዳቸው ከ14ሺህ ብር በላይ ገንዘብ መሰጠቱ ተመልክቷል።

የክፍለ ከተማው የምግብ ዋስትናና የልማታዊ ሴፍትኔት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስጨንቅ ብርሃኑ በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ በክፍለ ከተማው በኑሯቸው ዝቅተኛና አቅመ ደካማ የሆኑትን በመለየት በሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።

ለዚህ መልካም ተግባር ትብብር ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል፡፡

የሴፍትኔቱ ተጠቃሚዎች በከተማ ግብርና፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እና በደረቅ ቆሻሻ ማሰባሰብ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

በተለያዩ አደረጃጀቶችም ከሥራቸው ባለፈ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያዳብሩ ሲሰራ መቆየቱን ነው የገለጹት።

"በዚህም በዕድርና በዕቁብ እንዲሁም በባንክ የገንዘብ ቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ተደርጓል" ብለዋል።

ይህም የተሻለ ውጤት እንደተገኘበት የገለጹት ኃላፊው፣ በቀጣይም ለሚሰማሩበት ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ የክህሎት ስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ለእዚህም ክፍለ ከተማው በማኑፋክቸሪግ፣ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽንና በንግድ ሥራ ላይ ከኮሌጆች ጋር በመተባበር ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ መሆናቸውንና ወደ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ለመሸጋገር የተዘጋጁት ወይዘሮ አበበች ስንታየሁ ቀደም ሲል ሥራ በማጣት በቤት ውስጥ እንደሚውሉና በእዚህም ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል።

በመንግስት በተመቻቸላቸው ሥራ ሰርተው ባገኙት ገንዘብ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር በመቻላቸው አመስግነው፤ በቀጣይ ለሚሰማሩበት ሥራ በቂ የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል

በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ሲሰማሩ የመንግስት የገንዘብና የስልጠና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው የጠየቁት፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 15 ወረዳዎች ከ63 ሺህ በላይ ሰዎች የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ እንደሆኑ ከፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም