ያልታሰበው ድምፅ

3605

 የጸዳወርቅ ታደለ /ኢዜአ/

ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ዕለተ እሁድ ማለዳ። በስራዬ ባህርይ ምክንያት ቅዳሜና እሁድም ሆነ የበዓል ቀናት የሥራ ቀናቶቼ ናቸው። ይሄኛው እሁድ ግን የዕረፍት ቀኔ ነበር። ከእንቅልፌ ብነቃም ከአልጋዬ አልወረድኩም።

ከማለዳው 12 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ ተንቀሳቃሽ ስልኬ ጥሪ አሰማ። እናቴ ነበረች። ድንገተኛ ጉዳይ ካልገጠማት በስተቀር በዚህ ሰዓት እንደማትደውል ስለማውቅ ድንጋጤ ብጤ ተሰማኝ።

በአግባቡ መናገር አልቻለችም። ድምጿ በለቅሶ ሲቃ ተይዞ ይቆራረጣል። በቅጡ ልታናግረኝ አልቻለችም። የሆነ ችግር እንዳለ ተሰማኝና የማልደብቀው ዓይነት ድንጋጤ መላው አካሌን ወረረው።

ከሞቀው አልጋዬ ተስፈንጥሬ ስወረድ የማስታውሰው አንድም ነገር አልነበረም።  ከድምፄ መለወጥ ድንጋጤዬን የተረዳችው እናቴም እራሷን አረጋግታ እኔኑ ማረጋጋት ያዘች።

በከፍተኛ ሲቃ የተሞላቸው በደስታ ብዛት እያለቀሰች መሆኑን ገለፀችልኝ። ወዲያውኑም ድንጋጤዬ ወደ ጉጉት ተለወጠ። በደስታ ለቅሶ የሞላትን ብስራት የማወቅ ጉጉት።

“የልጅነት አገር ቤተሰቦቼን አየኋቸው” አሁንም በእምባ ሲቃ በሚቆራረጥ ድምፅ።  ግራ ተጋባሁ።

“በአሁኗ ቅፅበት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኤርትራ መዲና አስመራ ናቸው። የአስመራ ህዝብም በእልልታ እየተቀበላቸው መሆኑን በኤርትራ ቴሌቭዥን በቀጥታ እየተላለፈ ነው፤” የሚሉ በደስታና ለቅሶ የተሞሉ ቃላቶችን አዘነበችብኝ።

ምላሼን ሳትጠብቀ ንግግሯን ቀጠለች። “ዘወትር ዓይኑን ለማየት እናፍቀው የነበረውን አባቴን በሞት ብነጠቅም ለዓመታት በአካል ርቀውኝ ስናፍቃቸው የኖሩትን ወንድሞቼን ግን ያገኘኋቸው መስሎ ተሰማኝ፤ እናም በደስታ አለቀስኩ” ስትል ነገረችኝ።

እናቴና በኤርትራ የሚኖሩት የምትወዳቸው ቤተሰቦቿ ከተለያዩ ሁለት አስርት ዓመት ሆኗል። ይህ ታሪክ ገና ህፃን ሳለሁ ጀምሮ የምሰማው የእናቴ የእለት-ተእለት ትርክት ነበር።  በተለይ እናቴ ከወንድሞቿ በተለየችበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በገፅታዋ ላይ ይነበበ የነበረው የሀዘን ስሜት አሁንም ድረስ ከአእምሮዬ አይጠፋም። ታሪኩን ስታስታውሰኝ ከፊት ለፊቴ የመጣው ምስልም ይኸው የሚያሳዝነው የውዷ እናቴ የተከፋ የፊት ገፅ ነው።

ከእናቴ ጋር የነበረኝን የትዝታና ደስታ ቆይታ በማቋረጥ በፍጥነት ያመራሁት ወደቴሌቪዥኑ መስኮት ነው። ለካስ ኤሌክትሪክ ተቋርጧል። ወሽመጤ ተቆረጠ። ሌላ አማራጭ ወደአእምሮዬ መጣ። የተንቀሳቃሽ ስልኬን ኢንተርኔት በመጠቀም ማህበራዊ ሚዲያዎችን መጎብኘት ጀመርኩ። ወሬው ሁሉ ኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ሆኗል። ድረ-ገጾች በኤርትራና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎች አሸብርቀዋል። የሁለቱን “አንድነትና መደመርን” የሚሰብኩ በርካታ ጽሁፎች ተለጥፈዋል።

እኔ ገና ከአልጋዬ ሳልወርድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማልደው ኤርትራ ምድር ውቢቱ አስመራ ተገኝተዋል። ማመን አልቻልኩም፤ በእጅጉ ተገረምኩ።

መደመሜን ቀጠልኩ። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጎን ለጎን ቆመው የሚያሳይ ምስል ሳይ ሰውነቴን አንዳች እንግዳ ስሜት ወረረው።

በህፃንነቴ እንደዘበት አደምጠው የነበረው የእናቴ ወንድሞች (አጎቶቼ) እና ቤተሰቦቻቸው ጉዳይ በተለየ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይመላለስብኝ ጀምሯል። የስጋ ዘመዶቼ ወንድምና እህቶቼ ናቸው። ማንነታቸውን፣ እንዴት እንደሚኖሩ ስንት ልጆች እንዳሏቸው ወዘተ የማውቀው አንዳችም ነገር የለም። እናም የእናቴን ያህል እንኳ ባይሆን የተለያየኋቸውን ስጋ ዘመዶቼን በቅርቡ ለማየት የታደለኩ መሆኑን ሳጤን ለመጀመሪያ ጊዜ የእውነት ጓጓሁ።

ከደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ መብራት መጣ። የቴሌቪዥኑ መስኮት ተከፈተ። አስመራ ከተማ በውብ የኤርትራ ልጆች፣ እናቶች፣ አባቶችና ወጣቶች ደምቃለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ባሉት መሰረት ኤርትራ መክተማቸውና የሰላም ጠያቂ ብቻ ሳይሆኑ የሰላም አክባሪና ተግባሪ መሆናቸው እየተገረምኩ ደግሜ ለእናቴ ደወልኩላት።

“ሁሉን ነገር ቀኑን ጠብቆ ይሆናል፤ እኔ የአባቴንና የሁለት ወንድሞቼን ዓይን ሳላይ ሞት ነጠቀኝ። እናንተ እድለኞች ናችሁ። ዘወትር የምፀልየው በኤርትራ ከሚኖሩት የወንድሞቼ ልጆች ወንድሞቻችሁ በዓይነ ስጋ ሳላገናኛችሁ እንዳልሞት ነበር፤ ጸሎቴ ሰምሯል፤” አለችኝ አሁንም የደስታ ሲቃ እየተናነቃት።

ይህ የእኛ ቤተሰብ ታሪክ የሌሎች አያሌዎች ታሪክም ነው። ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ አገሮች መካከል የቆየው የጠላትነት ግንኙነት ባልና ሚስትን፣ ወላጅና ልጅን ጨምሮ በርካታ ዘመድና ወዳጆችን አራርቋል፤ አቆራርጧል።

በዚህ ፍጥነት ይሆናል ተብሎ ለመገመት የሚያዳግተው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ህልም በሚመስል መንገድ እየተለወጠ ነው።

አሁን እናቴና ለዓመታት የናፈቀቻቸው ዘመዶቿን በፈለገችው መንገድ ማግኘት ትችላለች። አዲስ አበባ እና አስመራ በተንቀሳቃሽም ሆነ በመደበኛ ስልክ፣ በአየርም ሆነ በየብስ ትራንስፖርት እንዲገናኙ መሪዎቻቸው ወስነዋል። የስልክ ገመዱ በተቀጠለበት ዕለተ የተወሰኑትን የወንድሟን ልጆች ድምፅ መስማት ችላለች። በደስታ እንባም ተራጭታለች።

ከ54 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ እናቴ ጋር የነበረኝን ወግ ቀጠልኩ።

“እንደዚህ ዓይነቶቹን ቀናት ታሪካዊ አድርጎ መመዝገብ ይገባል። በእድሜዬ ሙሉ ይህንን ታሪካዊ ቀን ስናፍቅ ኖሬያለሁ፤ መሪያችን ዶክተር አብይ አህመድ ይህ እውን እንዲሆን ፈር ቀዳጅ በመሆኑም ኮርቻለሁ፤ ይህ ስሜት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ እንዳለ ባምንም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እየዳበረ እንዲቀጥል በተለይ ለወጣቱ የፍቅርና መተሳሰብ መንፈስ አብዝቶ ይስጥልኝ”  በማለት ሀሳቧን ቋጨች።

ይህ አስደማሚ ታሪክ ቀጥሏል። ዛሬ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓም ዕለተ ቅዳሜ ሁለተኛዋ የተስፋና የደስታ ቀን ተብላለች። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ገብተዋል።

አዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿም ፕሬዝዳንቱን በድምቀት ተቀብለዋቸዋል።

የሁለቱ አገራት ፍቅር ለምልሞ እናቴንና እንደሷ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ጸሎታቸው ሰምሮ ይህን ስላዩ እንኳን ደስ አላቸው እንኳን ደስ አለን።