ተስፋ ደርጅት በተለያየ ሙያ ያሰለጠናቸውን 198 ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎች አስመረቀ

61
አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2010 ወይዘሮ ረድኤት ታረቀኝ ኑሯቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ከሚገፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናቸው። እኚህ እንስት ከድህነት ጋር በተያያዘ የሚገጥማቸውን የህይወት ውጣ ውረድ ለማሸነፍ የሚያግዛቸው ትምህርትም ሆነ ምንም ዓይነት ሌላ ክህሎት አልነበራቸውም። በመሆኑም ለረጅም ዓመታት የእርዳታ እጅ እየጠበቁ ለመኖር ተገደዋል። ዛሬ ግን ይህ ህይወት የሚያበቃበት አጋጣሚ መፈጠሩን ወይዘሮ ረድኤት ይናገራሉ። በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ ተግባሩ የሚታወቀው አገር በቀሉ ግብረ ሰናይ "ተስፋ ድርጅት" ባደረገላቸው ድጋፍ የክህሎት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። የተስፋ ድርጅት አዲስ አበባ ቅርንጫፍ በቴክኒክና ሙያ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ በመደበኛና በአጫጭር መርሃ ግብር አሰልጥኖ ዛሬ ካስመረቃቸው 198 ሰልጣኞች መካከል ወይዘሮ ረድኤት አንዷ ናቸው። በምግብ ዝግጅት ሙያ ሰልጥነው ስራ የሚያስገኝ ሙያተኛ የሆኑት ወይዘሮ ረድኤት "ከዚህ በፊት በአስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ነው ኑሮዬን የገፋሁት፤ አሁን ግን ድርጅቱ ባደረገልኝ ድጋፍ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለሙያ ለመሆን በቅቻለሁ፤ ወደ ስራ ልገባ እንደምችልም ተስፋ አለኝ፤" ሲሉ ገልፀዋል። "እንደ እኔ ያሉና በአስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያሳለፉ ሴቶች ወደ ፊት በመምጣት መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን በራሳችን መፍታት እንችላለን" በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። ከዚሀ በፊት ወደ አረብ አገር ተሰዳ ትኖር እንደነበር የምትናገረው ሌላዋ ሰልጣኝ ወይዘሪት ሰናይት አበሻ ደግሞ የልብስ ስፌት ባለሙያ ለመሆን በቅታለች። በሰለጠነችበት ሙያ ተሰማርታ ራሷን በመቻል ለሌሎች በአረብ አገሮች በስደት ለሚኖሩ ወገኖቿ እና ከስደት ተመላሾች አርኣያ መሆን እንደምትሻ ተናግራለች። ድርጅቱ ዛሬ ያስመረቃቸው 99 ወንዶችንና 99 ሴቶችን ሲሆን የስራ እድልም የተመቻቸላቸው መሆኑ ተጠቁሟል። ተመራቂዎቹ የሰለጠኑት በእንጨት ሙያ፣ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ በምግብ ዝግጅትና በልብሰ ስፌት የስራ ዘርፎች ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 128 የሚሆኑ ለስደት ተጋላጭ የነበሩ ወጣቶችን ተቀብሎ በተለያየ ሙያ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፎች ያሉት ተስፋ ድርጅት ከ3 ሺህ የሚልቁ ዜጎችን በቋሚነት በመደገፍ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም