የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 16 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በጀት አጸደቀ

64
ጂግጂጋ ሀምሌ 7/2010 የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2011 የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ 16 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር  በጀት አጸደቀ፡፡ ለምክር ቤቱ ረቂቅ የበጀት አዋጁን ያቀረቡት የክልሉ ፋይናንና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አብዲ እንደገለጹት የፀደቀው በጀት ለአዲስና ለነባር ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንዲሁም ለመደበኛ ስራዎች የሚውል ነው፡፡ ከፕሮጀክቶቹ መካከል የዋቢ ሸበሌ ወንዝ የሚያስከትለው አደጋ መከላከል፣ የስራ እድል ፈጠራ ፣ የቤቶች ልማትና ባለፈው የበጀት ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የተያዘ ነው፡፡ የበጀቱ ምንጭ የፌዴራል መንግስት ድጎማ ፣ በክልሉ የሚሰበሰብ ገቢ ፣ ብድርና ካለፈው ዓመት የዞረ መጠባበቂያ ገንዘብ መሆኑን አቶ አህመድ አስታውቀዋል፡፡ ለበጀት ዓመቱ የተመደበው ይሄው ገንዘብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ1ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር  ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ የምክር ቤቱ  አባል ወይዘሮ ቃሊ አብዱላሂ በሰጡት አስተያየት ለልማት የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ከክልሉ ኦዴት ቢሮ እና ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋልል፡፡ የጸደቀው በጀት የዋቢ ሸበሌ ወንዝ በየዓመቱ የሚያስከተለውን ጎርፍ ለመከላከል  የሚያስችሉ ስራዎች እንዲከናወኑና ሌሎችን ስራዎች ተፈጻሚነታቸውን በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሰዓዲያ መሀመድ ናቸው፡፡ ጉባኤው የተጠናቀቀው በበጀት ዓመቱ የክልሉ የልማት ክንዋኔዎችን ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ኦዴት መስሪያ ቤት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ በመወያየትና በማጽደቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም