ከቡና ብዛት ይልቅ ጥራት ላይ አተኩረን በመስራታችን ይበልጥ ተጠቃሚ ሆነናል - ተሸላሚ አርሶ አደሮች

109

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/2013 (ኢዜአ) ከቡና ብዛት ይልቅ ጥራት ላይ አተኩረው በመስራታቸው ይበልጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን የልዩ ጠዓም ቡና ተሸላሚ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በቡና ልማት የተሰማሩ ሌሎች አርሶ አደሮችም ከምርት ብዛት ይልቅ ለጥራት ትኩረት ቢሰጡ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መክረዋል።

ባለፈው ዓመት በልዩ ጠዓም የቡና ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ) ተሳትፈው ያሸነፉ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት ቡናን በብዛት ከማምረት ይልቅ ለጥራት ትኩረት ሰጥተው ማምረት ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መጥቷል።

ቡናን በጥራት ማምረት ለአርሶ አደሩም ሆነ ለአገር የሚሰጠው ጥቅም የተሻለ በመሆኑ በቀጣይ ለምርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩና ሌሎች አርሶ አደሮችም ቡናን በጥራት ቢያመርቱ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡናን በብዛት ብቻ ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት ለራስም ሆነ ለአገር የሚሰጠው ጥቅም አነስተኛ እንደሆነ መረዳት እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

ቡና አምራች አርሶ አደሮች ቀያይ የቡና ፍሬዎችን ብቻ በመልቀም ለገበያ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያመለከቱት።

በ2012 ዓ/ም በተካሄደው የልዩ ጠዓም ቡና ውድድር አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ መሆናቸውን የገለጹት በሲዳማ ክልል ጉራ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ንጉሴ ገመዳ፣ አንድ ኪሎ ግራም ቡና እንደደረጃው እስከ 13 ሺህ ብር መሸጣቸውን ተናግረዋል።

በውድድሩም 1ሺህ 244 ኪሎ ግራም ቡና በማቅረብ የተሳተፉ ሲሆን ካቀረቡት ቡና እስካሁን ድረስ 540 ኪሎ ግራም መሸጡንና ከዚህም 5 ሚሊዮን 930 ሺህ ብር ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

"በተለይ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ከልዩ ጠዓም ቡናወዳዳሪዎች ጋር በመተባበር በቡና ጥራት ላይ አተኩሮ የተሰጠው ስልጠና ውጤታማ እንዲሆን ረድቶኛል" ብለዋል፡፡

የደረሱ ቡናዎችን ብቻ በመልቀምና ለጥራት ትኩረት በመስጠት ገበያውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ የተናገሩት አርሶ አደር ንጉሴ ባላቸው 10 ሄክታር የቡና ማሳ ላይ ጥራት ያለው ቡና በማምረት በቀጣይም ተሸላሚ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከምዕራብ አርሲ ዞን ኮኮሳ ወረዳ በቡና ልማት ሥራ የተሰማሩት አርሶ አደር ብርሃኑ ተክሉ በበኩላቸው፣ በልዩ ጠዓም ቡና ውድድር ጥራቱን የጠበቀ 1ሺህ 240 ኪሎ ግራም ቡና በማቅረብ አራተኛ መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለገበያ ካቀረቡት ቡና ውስጥ 600 ኪሎ ግራም ቡና ተሽጦ ከ53 ሺህ 439 ዶላር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ቡና አምራች አርሶ አደሮች ከዘልማድ አሰራር ወጥተው የቡናን የጥራት ደረጃ በማሻሻል የበለጠ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው አርሶ አደር ብርሃኑ የመከሩት።

ከዚህ ቀደም በብዙ ልፋት በርካታ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ ያገኙት የነበረ ገቢ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው፣ "በጥራት መስራት ከትንሽ ምርት ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል በራሴ አይቼዋለሁ" ብለዋል፡፡

ቡና ከአተካከል ጀምሮ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት አርሶ አደር ብርሃኑ፣ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ከልዩ ጠዓም ቡና አወዳዳሪዎች ጋር በመሆን የሰጣቸው ስልጠና ለውጤት እንዳበቃቸውና ስልጠናውም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ኡመር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቡና የተፈጥሮ ቡና ጣዕም ያለው ቢሆንም ከዚህ ቀደም ቡናው ይሸጥ የነበረው በርካሽ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በቡና ማሻሻያ አዋጁ መሰረት የቡና መሸጫ ዝቅተኛ ዋጋን በማስቀመጥ የተሻለ ገቢ እየተገኘ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ባለፈው ዓመት በልዩ ጠዓም የቡና ውድድር 39 አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ወደውጭ ልከዋል።

አንድ አርሶ አደር የቡና ምርቱን በኪሎ እስከ 13 ሺህ ብር ለመሸጥ መቻሉንም ገልጸው፣ ይህም የኢትዮጵያ ቡና ምን ያህል ጥራት እንዳለው ለዓለም ገበያ ያስተዋወቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተሻለ ገቢ እየተገኘ መምጣቱን ጠቅሰው፣ የቡናን ጥራት ለማስጠበቅ በሚሰራው ሥራ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ2 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ስልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም