አንዱ የሌላውን ባህልና ወግ ማክበር ለጠንካራ ሃገራዊ አንድነት ጠቃሚ ነው…የሆራ አርሴዲ ኢሬቻ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
አንዱ የሌላውን ባህልና ወግ ማክበር ለጠንካራ ሃገራዊ አንድነት ጠቃሚ ነው…የሆራ አርሴዲ ኢሬቻ ተሳታፊዎች

ቢሾፍቱ፣ መስከረም 24/2013(ኢዜአ) አንዱ የሌላውን ባህልና ወግ ሲያከብር ጠንካራና አንድነቷ የተጠበቀ አገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያጎለብት መሆኑን ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የመጡ የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ ታዳሚዎች ተናገሩ።
የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በተከበረ በማግስቱ የሚከበረው የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዋዜማው በደራው የባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ ሽያጭ ነበር ቢሾፍቱን ማድመቅ የጀመረው።
የገዳን ስርዓት በተከተለው የአባ ገዳዎች ባህላዊ ዜማና ምርቃት ማልዶ በተከፈተው የዘንደሮው የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል እንደወትሮው በሚሊዮኖች ሳይሆን አባ ገዳዎች ባስቀመጡት ምክር በውስን ሰዎች ነው በዓሉ የተከበረው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የበዓሉ ተሳታፊዎች እንዳሉት ከሀገር አልፎና እራሱን ችሎ በዓለም ቅርስነት በመመዝገብ ላይ ያለው ኢሬቻ ውብና ብሔር ብሔረሰቦችን የሚያቀራርብ በዓል ነው።
በመሆኑም ኢሬቻን ጨምሮ ሌሎች በሔሮችን የሚያቀራርበውን በዓል በአብሮነት ማክበሩ ለአገሪቷ አንድነት የጎላ ሚና አለው።
ከሃዲያ ዞን የመጣችው ወጣት ቤተልሔም አሰፋ እንዳለችው አንዱ ያንዱን ባህል ሲያከብር ትስስሩን በማጥበቅ የኢትዮጵያን አንድነት ያጠናክራል።
ከምዕራብ ጉጂ ዞን የመጣው አቶ ኤቢሳ በላይም “ኢሬቻ ትልቅ ትርጉም ያለውና ሁሉም ብሔረሰቦች መጥተው በደስታ የሚካፈሉት በዓል ነው፤ ይኸ ደግሞ አንድነትን ያጠናክራል” ብለዋል።
ሴሌሜ ሴሌሜን በመጨፈር ሲያደምቁ ከነበሩ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ቴዎድሮስ ደረሰም ከሃዲያ ዞን ነው የመጣው።
ወጣቱም በተለይም መሰል በዓላት የተራራቁትን ያቀራርባል፣ ይቅር ይባባሉበታልም ይህም ለአንድነቱ ብዙ ጥቅም አለው ብሏል።
አቶ አብርሃም ወንድሙም ከአዳማ በመምጣት ነው በዓሉን የሚሳተፈው።
ለማንም የማይመለሰው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሰውን ቁጥር ቢያሳሳም ኮቪዱ ጠፍቶ ሰው እንደ ድሮው ጋራውን ሸፍኖ የምናከብርበት ጊዜ እንደሚመጣ ምኞቴ ነው ብለዋል።
አቶ አብርሃም አክለውም ኢሬቻ ከኦሮሞ አልፎ ፈረንጅ የሚሳተፍበት በመሆኑ ሁሉንም በአንድ የሚሰበስብና ትስስር የሚፈጥር ነው ብለዋል።