በምዕራብ ሃረርጌ ዞን መኤሶ ወረዳ የተከሰተው ግጭት ወደ መረጋጋት እየተመለሰ ነው...የዞኑ ጸጥታ ጽሕፈት ቤት

69
ጭሮ ሀምሌ 7/2010 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ ከትላንት ጀምሮ የተከሰተውን ግጭት ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደርና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። በግጭቱ አምስት የጸጥታ አካላት ሲሞቱ ከሰባት በላይ መቁሰላቸውንም ጽሕፈት ቤቱ አመልክቷል። የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ ጽፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኃይሌ ዴቲ እንደገለጹት የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በማይሹ አካላት የተነሳውን ግጭት ለማርገብ የኦሮሚያ ፖሊስና የጸጥታ አካላት የማረጋጋት ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ። በሁከቱ የተፈጠረው አለመረጋጋትም ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሚኤሶ ከተማ ነዋሪዎች በስጋት ላይ መሆናቸውን ገልጸው የጸጥታ ኃይሎች ባደረጉት የተጠናከረ ትግል ወረዳው ወደ መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን ተናግረዋል። በግጭቱም አምስት የጸጥታ አካላት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በተጨማሪም ሰባት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸው አካባቢው በአሁኑ ወቅት ወደ መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን ገልጸዋል። ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ሆን ብለው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አካላት ስላሉ መንግስት ከኦሮሚያም ሆነ ከሶማሌ ክልል በኩል መሰል ተግባር የሚፈጽሙትን አካላት በመለየት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ተናግረዋል። መንግስት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች  ያለውን ሰላም ለማስጠበቅና የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑ ይታወሳል፡፡  በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን ሰላም ለማስጠበቅና የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር የሚረዳ የጋራ የሰላም ኮንፍረንስ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ ቀደም ሲል መከናወኑን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም