ቸሻየር ኢትዮጵያ የሀዋሳ ማዕከል ለ293 አካል ጉዳተኞችና ቤተሰቦች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

1050

ሀዋሳ መስከረም 22/2013 (ኢዜአ) ቸሻየር ኢትዮጵያ የሀዋሳ ማዕከል የኮሮና ወወርሽኝ ጫና ላሳደረባቸው 293 አካል ጉዳተኞችና ቤተሰቦች ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግባና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ ፡፡ 

የማዕከሉ  ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳግም ጌታሁን በድጋፍ አሰጣጡ ስነስርዓት እንዳሉት ድርጅቱ በዋናነት አካል ጉዳተኞች በማንኛውም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚሰራ ነው፡፡

ለዚህም የጤናና የአካል ተሀድሶ አገልግሎት፣ የትምህርተና ሥልጠና፣ የምክር አገልግሎትና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ አካል ጉዳተኞች ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ እየሰራ ነው ብለዋል።

በሀዋሳና አካባቢው ባሉ ከተሞችና ወረዳዎች ለሚገኙ አነስተኛ ገቢ ላላቸው 293 አካል ጉዳተኞችና ቤተሰቦች  

ለአራት ተከታታይ ዙር የምግባና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው  ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል ፡፡

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የማህበራዊ ደህንነት ልማት ሥራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሮ አስቴር ግዛው በበኩላቸው አካል ጉዳተኞችና ቤተሰቦች በወረርሽኙ ምክንያት ለጉዳት እንዳይጋለጡ ያበረከተላቸው ድጋፍ ለከተማ አስተዳደሩ ትልቅ እገዛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለወደፊትም ትብብር በሚሹ የማህበረሰብ ልማት ሥራዎች ላይ ከማዕከሉ ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች መካከል ወይዘሮ ነኢማ ከድር በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ ከዚህ በፊትም የስፌት ሥራ ሥልጠናና የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ሶስት ልጆች እናዳሏቸው የተናገሩት  ወይዘሮ ነኢማ “የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ እኔና ባለቤቴ የምናገኘው አነስተኛ ገቢ በመቀዛቀዙ ለችግር ተጋልጠን ነበር “ብለዋል፡፡

የማዕከሉ  ድጋፍ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ እንደረዳቸው ገልፀው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ወይዘሮ መስታወት ታደሰ በበኩላቸው የሁለት አካል ጉዳተኛ ልጆች እናት እንደሆኑ ጠቅሰው በዚህ ወረረሽኝ ወቅት አካል ጉዳተኛ ልጆችን ጠብቆ ማሳደግ በራሱ ፈተና ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ በተደጋጋሚ ያደረገላቸው ድጋፍ ወረርሽኙ ያሳደረባቸውን ጫና እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡