በኢትዮጵያ 34 አዲስ ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ`ኃይል

533

አዲስ አበባ መስከረም 21 /2013(ኢዜአ) መላው ኢትዮጵያ 34 አዲስ ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታወቁ።

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ሶስት ከተሞች በ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነቡ ሶስት ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ በቢሾፍቱ፣ዱከምና ሞጆ የተገነቡትን  ጣቢያዎች መርቀው ከፍተዋል።

የቢሾፍቱ ከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ባለ 400/230/15 ኪሎ ቮልት የሚያከፋፍል ሲሆን፤ 33 ነጥብ 2 ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።

የዱከም ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት ኃይል ማከፋፊያ ጣቢያ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።

የሞጆ 230/15 ኪሎ ቮልት ማከፋፊ ጣቢያ 11 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎባቸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተመረቁት የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያዎች ለኢንዱስትሪዎች ተደራሽነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብና የኃይል መቆራረጥና ጫና ለማስቀረት ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 34 አዲስ ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙአስታውቀዋል።

ጣቢያዎቹ ከ2008 ጀምሮ በመገንባት ላይ እንደሚገኙና በቀጣዩ ግንባታቸው ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ጣቢያዎቹ ከሶማሌ፣ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ውጭ ያሉትን ክልሎች የሚያዳርሱ ናቸው ብለዋል።

የጊንጪ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ጨምሮ አራት ማከፋፈያ ጣቢያዎች በያዝነው ዓመት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የጣቢያዎቹ  ግንባታ ከውጭ መንግሥታትና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሚገኝ ብድርና በኢትየጵያ መንግሥት ወጪ እንደሚሸፈን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትና በአምስት ዓመት ውስጥ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የአዳዲስ የማከፋፊያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መሥመሮች መገንባት ሚና ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ጣቢያዎቹ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ ከተመረቁት ጣቢያዎች በተጨማሪ በክልሉ የማከፋፈያ ጣቢያዎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የብልጽግናን ጉዞ ከሚያሳኩ ዋና ጉዳዮች መካከል መሰረተ ልማት አንዱ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት የብልጽግናን ጉዞ ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የተገነቡትን የኤሌትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት ሊንከባከባቸውና ሊጠብቃቸው እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ለማሻሻል እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መስፋፋት ኃይል ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋትና ያልተቋረጠ ኃይል ለማግኘትም  ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይልን አቅርቦት የሚያሰፋ መሰረተ ልማትን መገንባትና ኃይሉን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ ጥረቱ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይልን አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ አሰራርና ጊዜው የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በግንባታው ለተሳተፉ ተቋራጮች፣አማካሪዎች ሰራተኞችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሶስቱ ጣቢያዎች ግንባታ በሕንድ፣በቦስኒያ ሄርዞጎቢኒያና በኢትዮጵያ  ሥራ ተቋራጮች  መከናወናቸው በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ  ተገልጿል፡፡

በአማካሪነት ደግሞ የጀርመንና ስዊዘርላንድ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የጣቢያዎቹ ግንባታ  ከፈረንሳይ ልማት ባንክ በተገኘ 85 በመቶ ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት 15 በመቶ ወጪ ተከናውኗል።

በግንባታው የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂናዕውቀት ሽግግር እንዲሁም ለቀጣይ ሥራ ልምድና ተሞክሮ ያገኙበት ነበርም ተብሏል።