የደቡብ ክልል የሠላም ምክር ቤት ተቋቋመ

105

ሀዋሳ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የሠላም ምክር ቤት ዛሬ ተቋቋመ ፡፡

ለግማሽ ቀን በተካሄደው ስብሰባ ለተቋቋመው ምክር ቤት  15 አባላት ያሉት ሥራ አስፈፃሚዎችም ተመርጠዋል።

በዚህ ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ሠላም ሲጠፋ ብቻ ሳይሆን ያለውን ሠላም አጠናክሮ ለማስቀጠልና ሥጋቶችን አስቀድሞ ለማስወገድ ሁል ጊዜም ስለሠላም መምከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የሠላም ጉዳይ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል ፡፡

ሠላምን ማረጋገጥ ከተቻለ ሁሉንም አይነት ፍላጎቶች ማሳካት እንደሚቻል የተናገሩት አቶ ርስቱ በዚህ ረገድ አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የኃይማኖትና የባህል መሪዎች ፣ ምሁራን ፣ ወጣቶችና የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ፡፡

ለዚህም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የሠላም ምክር ቤት ማቋቋም ማስፈለጉን ተናግረዋል ፡፡

ምክር ቤቱ ሠላም ሲደፈርስ ብቻ ሳይሆን ግጭት ከመፈጠሩ አስቀድሞ በመምከር የመፍትሔ ሀሳቦችን የሚያመጣ፣ በህዝብና መንግስት መካከል የመልካም ግንኙነት ሥርዐት የሚዘረጋ እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡

የሠላም ምክር ቤቱ ከክልል እስከቀበሌ ባሉ መዋቅሮች እንደሚቋቋምም ጠቁመዋል ፡፡

ሌላው ተሳታፊ የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር እንድርያስ ጌታ በበኩላቸው የሠላም ዋጋን በሚገባ የምንረዳው ሠላም በምናጣበት ወቅት ነው ብለዋል ፡፡

በሀገርም ሆነ በክልሉ ተከስተው በነበሩ የፀጥታ ችግሮች በሰውና ንብረት ላይ ያስከተሉት ጉዳት ለዚህ ማሳያ እንደነ ጠቅሰዋል ፡፡

በሠላም ግንባታ ላይ ሁላችንም የበኩላችንን ካልተወጣን ለተወሰኑ አካላት ብቻ በመተው የምንፈልገውን ሠላም ማስፈን አንችልም ብለዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትና ስለአካባቢው ሠላም በጥልቀት መክረው መፍትሔ የሚያበጁበት ምክር ቤት መቋቋሙ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ ፀጋዬ ኦብሴ የምክር ቤቱ መቋቋም ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ተገቢና ወቅታዊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት አስቀድሞ መክሮ ለማምከን እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

እስካሁን በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ቀውሶች ዋንኛ ተዋናይ የነበረው ወጣቱ ነው ያለው ደግሞ የደቡብ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት ዘላለም ዘሪሁን ነው።

የተሻለች ሀገር የመፍጠር ኃላፊነትና አቅም ያለው ይሄው ወጣት መሆኑን ገልጾ የምክር ቤቱ መቋቋም ፌዴሬሽኑ የክልሉን ወጣቶች በማሳተፍ ለሚሰራው የሠላም ግንባታ ሥራ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው ብሏል።

በስነ-ስርዓቱ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ፣ ምሁራን ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የኃይማኖትና የባህል መሪዎች ፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም