ኢትዮ ቴሌኮም በዘርፍ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀቱን ገለጸ

85

መስከረም 21/2013 ( ኢዜአ)  ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ከሚመጡ ኦፕሬተሮች ጋር ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ኢትዮ ቴሌኮም ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በዘርፉ ካሉ ስራ ፈጣሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ ከመሰረተ ልማት እና ከሪፎርም ስራዎች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ብሄራዊ ብራንድ ከመሆኑ አንፃርና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በአገር ውስጥ ያሉ በዘርፉ የተሰማሩ ስራ ፈጣሪዎችን ከውጭ በሚመጡ ኩባንያዎችና ድርጅቶች እንዳይዋጡ መንግስት ድጋ እንዲያደርግ እና ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበት አቅም ቢጠር የሚሉ ሀሳቦችም ተነስተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ከሚመጡ ኦፕሬተሮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን እና በቅንጅት ለመስራት ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።

ገበያው ለውድድር ሲከፈት ከሚገኘው ትርፍ ለአገርና ህዝብ የመጥቀም ዓላማ ያለው በመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም ውድድሩን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት አድርጓል ብልዋል።

ከመልካም አጋጣሚዎቹ ባሻገር ይዞት ሊመጣ የሚችለውንም ተግዳሮት ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በርካታ የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል።

በተለይም የዲጂታል ኢኮኖሚው እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በዘርፉ ከፍተኛ ፍላጎት በመፈጠሩ ለኢትዮ ቴሌኮም መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

መንግስት ዘርፉን ለውድድር ክፍት ሲያደርግ ለኢኮኖሚው አስተዋፆ የሚያበረክቱ መተግበሪያዎችን የአገር ውስጥ የዘርፉ ባለሙያዎች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋቸው መሰረተ ልማቶች አማካኝነት ምንአልባትም ከሚመጡት የቴሌኮም አፕሬተሮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውን እቅም እየፈጠረ እንዳለ እና በቅንጅት ለመስራትም ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

የሚመጡ አፕሬተሮች የኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን በሊዝ የሚከራዩ ከሆነ ከ1 ነጥብ 6 እስከ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚገኝ መሆኑንም አመላክተዋል።

ለዚህም ደግሞ የተደረገው ዝግጅት ተወዳዳሪ ለመሆን እና በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በውይይቱ  ላይ በኢንፎርሜሽን ዘርፍ ከተሰማሩ አካላትና ኩባንያዎች በተጨማሪ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም