ኮሚሽኑ ከታክስ ይግባኝ ጋር ለተያያዙ 800 የሚጠጉ ፋይሎች ውሳኔ ሰጠ

418

አዲስ አበባ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ባለፈው በጀት ዓመት ለ793 ፋይሎች ውሳኔ መስጠቱን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከያዛቸው 800 ፋይሎች 793ቱ ላይ ውሳኔ አሳልፋል፡፡ 


ኮሚሽኑ ባለፈው በጀት ዓመት  አፈጻጸምና በ2013 ዕቅድ ላይ ዛሬ ተወያይቷል፡፡

የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው  በዚሁ ወቅት  አንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የክርከርና ሌሎች ሥራዎች በመዘጋታቸው ፋይሎቹ ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ፋይሎቹ ከ2007 ጀምሮ ሲንከባለሉ የቆዩና አዳዲስ ፋይሎች መሆናቸውንም  አብራርተዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዳኞች ፋይሎችን ቤታቸው ወስደው በመስራታቸው ውዝፍ ፋይሎች በሙሉ ውሳኔ አግኝተዋል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በ2011 በጀት ዓመት ለ987 ፋይሎች  ውሳኔ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ኮሚሽኑ ተደራሸነቱን ለማስፋትም ሥልጣኑን ለክልሎች ውክልና ሰጥቶ ለመስራት ከርዕሳነ መስተዳድር ጋር  እየተነጋገረ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የገነባው በጀት ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት  በቀጣዩ ወር  አገልግሎት እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በክልሎች የሚገኙ የፌዴራል ግብር ከፋዮች ጉዳያቸውን በኦንላይን ለመከታተል ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የተካፈሉ ዳኞች በሰጡት አስተያየት  ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥራቸውን በነጻነት በማከናወናቸው ፋይሎች ላይ ፈጥነው ውሳኔ ለመስጠት መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡