በጣና ሃይቅ ሙላት ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል

402

ጎንደር መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ጣና ሐይቅ ሞልቶ ባስከተለው የውሀ መጥለቅለቅ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።

ድጋፉ የሚደረገው በአደጋው ተፈናቅለው በ11 ጣቢያዎች ለተጠለሉ ከስድስት ሺህ በላይ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው እንደሆነ ተነግሯል ።

የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ አደጋ መከላከልና የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ አቶ አገኘሁ አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት  ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ተጨማሪ የቀለብና አልባሳት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ።

ለተፈናቃዮች ለቀለብ የሚሆን 217 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ ሩዝ፣ አተር ክክና  ሽሮ ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል።

ለለሊት መኝታ የሚሆኑ 130 ፍራሾችም እንደሚሰራጩ ጠቅሰዋል።

በሀይቁ ሙላት ባስከተለው የውሀ መጥለቅለቅ ማሳቸው ለተጎዳባቸው አርሶ አደሮችም የሚያስፈልገው ተተኪ ዘር እንዲቀርብ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል።

በክልሉ መንግስት አማካኝነት ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውሰጥ አንድ ሺህ ኩንታል የምግብ እህል፣ ሶስት ሺህ ሊትር ዘይት ጨምሮ የተለያዩ ምግቦች እንዲሁም 700  ብርድ ልብስና ሌሎች የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ለተፈናቃዮች መሰራጨታቸውን ቡድን መሪው አስታውሰዋል።

የማእከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው ሰብላቸው ለተጎዳባቸው አርሶ አደሮች አራት ሺህ 500 ኩንታል ተተኪ የሽምብራ ዘር ለማቅረብ ከአጋር አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር መልኬ ተዘራ በመንግስት በኩል የቀለብ እህልና የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ  እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።

“በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ የዘራሁት  ጤፍና በርበሬ  በውሀ መጥለቅለቅ ጉዳት ደርሶበታል” ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሞገስ አይሸሽም ናቸው።

የወደመባቸውን ማሳ ፈጥኖ በሚደርስ ሰብል ለመሸፈን የዘር ድጋፍ እንዲደረግላቸው አርሶ አደሩ ጠይቀዋል ።

በወረዳው በጣና ሀይቅ ሙላት ካስከተለው የዜጎች መፈናቀል በተጨማሪ አምስት ሺህ 589 ሄክታር ማሳ  ላይ የነበረ ሰብሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ከወረዳው አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያመላክታል ።