"አዩዳ ኢን አክሲዮን" የተባለ ድርጅት የ5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የኮቪድ 19 መከላከያ ቁሳቁስ አበረከተ

56

አዲስ አበባ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) "አዩዳ ኢን አክሲዮን" የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ለተለያዩ ተቋማት የአምስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የኮቪድ 19 መከላከያ ቁሳቁስ አበረከተ።

የሰላም ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮና የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት ናቸው።

በድጋፉ ድንኳን፣ ቬንቲሌተር፣ ማቀዝቀዣና የውኃ ታንከር እንዲሁም አልጋ፣ ፍራሽና አንሶላ፣ ሳኒታይዘርና የንጽሕና መጠበቂያዎች ይገኙበታል።

በኢትዮጵያ የአዩዳ ኢን አክሲዮን ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ አበበ ዋጋው "የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስ ለተቋማቱ አበርክተናል" ብለዋል፡፡

በቀጣይም ወረርሽኙን ለመካለከል ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎችን በመለየት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የሕግ ማስከበር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው አዩዳ አክሲዮን ኢትዮጵያ የያዘችውን የድህነት ቅነሳ በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

መንግሥት የወረርሽኙን ተፅዕኖ ለመቀነስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ላሳየው ቁርጠኝነት ምሥጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ ከአገር ውጭ የሚገቡ ዜጎችና በድንበር ኬላዎች ላይ የተሠማሩ የፀጥታ አካላት በወረርሽኙ ተጋላጭ እንዳይሆኑ መንግሥት የያዘውን ሥራ እንደሚግዝም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋች የተጎዱ ዜጎች መኖራቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ፍሬዓለም ድርጅቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ  ተወካይ  አቶ መለሰ ለሚ ክልሉ የወረርሽኙን ተፅዕኖ ለመቀነስ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ወቅት ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ  ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ኃይሌ በቀለ በበኩላቸው በዞኑ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ለመከላከል ድጋፉ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

አዩዳ ኢን አክሲዮን እ.አ.አ. በ2002 በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመረ ወዲህ ከተለያዩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ዜጎችን ተጠቃሚ የሚደርጉ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

መቀመጫውን በስፔን በማድረግ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 42 አገራት የተለያዩ የልማትና የስብዓዊ ድጋፎችን እያከናወነ የሚገኝ ግብረ ሠናይ ድርጅት ሲሆን የተመሠረተውም እ.አ.አ. በ1981 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም