የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

404

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) የብሄራዊ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲ እንዲሁም የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ።

የብሄራዊ ትራንስፖርት ፖሊሲ፣ የሎጅስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲ እና የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂን የሚመለከት ይፋዊ መርሀ ግብር እየተካሄደ ነው።


የትራንስፖርት ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት በአማካኝ አስር በመቶ የኢኮኖሚ እድገትና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እድገት ይመዘገብባቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ አገራት አንዷ ነች።


በተለይም የትራንስፖርት ዘርፉ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እንዲቻል ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቀረፃ ላይ በትኩረት ሲሰራ የቆየ ሲሆን እነዚህን ማዕቀፎች መሰረት በማድረግም ዝርዝር የ10 ዓመታት እቅድ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል። 


በዚህ ረገድ የብሄራዊ ትራንስፖርት ፖሊሲው መርህ ካደረጋቸው ጉዳዮች የዘርፉ አጠቃላይ ልማትና እድገትን የሚደግፍ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ ብሎም ከብክነትና ከአካባቢ ብክለት የፀዳ አገልግሎት መስጠት የሚሉት ይገኙበታል። 


የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና አገልግሎቶችን ተፈጥሮአዊ ሥነ ምህዳርን የማይጎዱ ማድረግ እንዲሁም ዘመናዊ፣ ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና ተደራሽ የማድረግና የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማበርከት የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።


በሌላ በኩል ብሄራዊ ሎጅስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲው ቀልጣፋ ውጤታማና አስተማማኝ የሎጅስቲክስ ሥርአት ማረጋግጥ መርህ ይዞ የተዘጋጅ መሆኑን ገልፀዋል።


የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂውም መንገዶችን ለሰዎች በሚመች ሁኔታ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይና ተደራሽነት፣ ፍትሀዊነትና ዘላቂ ልማትን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ነው የገለፁት። 


እነዚህን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመተግበር በቀጣይ ዓመታት አጠቃላይ የአገሪቱን የመንገድ ሽፋንና ጥራት ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ወደ ስራ ማስገባትና በርካታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና አገልግሎቶችን በማቅረብ በዘርፈ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ ገልፀዋል።


በመርሀ ግብሩ የህዝብ ተወከዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌደራልና የክልል አመራሮችና የልማት አጋሮችን ጨምሮ ሌሌችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።