ዳሽን ባንክ የአምስት ቢሊዮን ብር ኖቶች ማሰራጨቱን ገለጸ

59

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) ዳሽን ባንክ አምስት ቢሊዮን ብር አዲሱን የብር ኖቶች ማሰራጨቱን ፕሬዚዳንቱ አስታወቁ።

ባንኩ ከኖቶቹ ለውጥ ጋር  በተያያዘም  25 ሺህ አዳዲስ የባንክ አካውንት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሆኑም ገልጿል።

የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ አዲሱን የገንዘብ ለውጥና ለ''ገበታ ለሀገር'' ፕሮጀክት የሚያደርጉትን ድጋፍ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ባንኩ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በ425  ቅርንጫፎቹ ኖቶቹን  ማሰራጨቱን ገልጸዋል።

ከተሰራጨው ገንዘብ ውስጥ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በዚህም አዲሱን 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በማሰራጨት 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን አሮጌ ብር መሰብሰቡን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

አዲሱን የብር ኖት ለማሰራጨት ተሽከርካሪዎችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን መጠቀማቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከድሮው የውድድር መንፈስ ይታይባቸው የነበሩ ባንኮች በአዲሱ ብር ለውጥ ከሰባት ባንኮች ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ገንዘቡን ወደ ባንክ እንዲያመጣ እያስተማሩ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፣ በዚህም 25 ሺህ አዳዲስ የባንክ አካውንቶች ተከፍተዋል ብለዋል።

በተከፈቱት አካውንቶች ብቻ  ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መደረጉን ጠቁመዋል።

አዲሱንም ሆነ አሮጌውን ብር የሐሰት ኖቶች ለማቅረብ ሙከራ እንደሚደረግ ገልጸው፣

ባለሙያዎችም እንደዚህ ዓይነት ችግር እንዳይከሰት ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ሆኖም በባንኩ አንድ ቅርንጫፍ የሐሰት ኖት ተይዞ ጉዳዩ በሕግ እየታየ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የዳሽን ባንክ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን በመደገፍ ለጎርጎራ፣ ኮይሻና ወንጪ ፕሮጀክቶች 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም