የኢትዮጵያ አየር ኃይል ድርብ ተልዕኮዎችን አንግቦ እየሰራ መሆኑን ዋና አዛዡ ገለጹ

113

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአገርን ሉአላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ የተለያዩ ተልእኮዎችን አንግቦ እየሰራ መሆኑን ዋና አዛዡ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

በአቪዬሽን አካዳሚ የሚሰጠውን ዘመናዊ ስልጠናም ማስፋቱንም ገልጸዋል።

ሜጀር ጄኔራልይልማ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት አየር ኃይሉ የአገርን የአየር ክልል ከማስከበር በተጨማሪ የተለያዩ ተልዕኮዎችን በመወጣት ላይ ነው።

በአደጋ ወቅት ዜጎችን በመታደግ የአየር አምቡላንስ አገልገሎት መስጠት፣ አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በልማት ተግባራት በመሳተፍ ሕዝባዊነቱን በማሳየት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተቋሙ በኤርፎርስ አካዳሚው ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት በቴክኖሎጂ የታገዙ ስልጠናዎችን እያስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል።

ዋና አዛዡ እንደገለጹት ከአሁን ቀደም በውጭ አገር ብቻ ይሰጥ የነበረውን የደረጃ ዘጠኝ (ሌቭል 9) ስልጠናን በአካዳሚው ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል።

በዘመናዊ ሲኙሌተር (ምስለ በረራ) የተደገፈ ዘመናዊና ወጭ ቆጣቢ ስልጠና በየደረጃው ላሉት አብራሪዎቹና ሌሎች ተማሪዎቹ እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለበረራ ስልጠና የሚያገለግሉ አዳዲስና ዘመናዊ አውሮፕላኖች ተገዝተው መግባታቸውን የገለጹት ዋና አዛዡ፣ በመጪዎቹ 10 ዓመታት ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል ለመሆን በሚያስችል መሰረት ላይ ይገኛል ብለዋል።

አየር ኃይሉ ከአዲስ አበባ ፣ ከአዳማና መከላከያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአፍሪካ የተለያዩ አገሮች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና ሲሰጥ የቆየው የኢትዮጵያ ኃይል፤ አሁንም ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ከ15 በላይ አገሮች የስልጠና ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በደጀን አቪየሽን ኢንጂነሪንግም ከውጭ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ተዋጊ አውሮፕላኖችንና ሌሎችን የማደስ፣ አናሎግ የነበሩትንም ዲጅታላይዝ የማድረግ ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

አየር ኃይሉ አሁን ካሉት አራት ዋና ዋና የጦር ይዞታዎች (ቤዞች) በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለመገንባት ዕቅድም  መያዙንም ሜጀር ጄኔራል ይልማ አስታውቀዋል።

በሰው ኃይል ራሱን ለማጠናከር በቀጣይ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃንን ለመመልመል ማቀዱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ በ1922 ገብተው በጃን ሜዳና ሥጋ ሜዳ ያረፉት የመጀመሪያዎቹ አውሮፕላኖች የአየር ኃይሉ ንብረቶች እንደነበሩ ይነገራል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በርካታ ግዳጆችን በጀግንነት እየፈፀመ ከዘመኑ ጋር እየዘመነ የቀጠለ አገራዊ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም