በ2012 በጀት ዓመት ከመንግስት የልማት ድርጅቶች 8 ነጥብ 67 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

66

አዲስ አበባ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በ2012 በጀት ዓመት ከመንግስት የልማት ድርጅቶች 8 ነጥብ 67 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን ገለጸ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረመስቀል እንደገለጹት፤ በኤጀንሲው ስር 21 የልማት ድርጅቶች አሉ።

የልማት ድርጅቶቹ ከውጭ ምንዛሬ ገቢው በተጨማሪ ባለፈው በጀት ዓመት 300 ቢሊዮን ብር ያህል ገቢ ያገኙ ሲሆን ከታክስ በፊት 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ገቢው የተገኘው ከምርት፣ ከሽያጭና ከአገልግሎት እንደሆነም አመልክተዋል።

ኤጀንሲው በ2012 በጀት አመት ወደ ግል ከተዛወሩ ድርጅቶች 330 ሚሊዮን ብር ሰብስቧል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት ሐምሌና ነሐሴ ወራት ብቻ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የዋና ሽያጭ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ቅጣትና ወለድ ምህረት መደረጉን ገልጸዋል።

በኤጀንሲው ስር ከሚገኙ 21 የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በስተቀር ሁሉም ትርፋማ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም