የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በምርምር መረጃ አቅርቦት ዘርፍ የተለያዩ ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑን ገለጸ

86

አዲስ አበባ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በምርምር መረጃ አቅርቦት ዘርፍ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት፣ ስልጠናና የምርምር ስራዎችን የሚያግዙ መረጃዎችን እየሰበሰበ እንደሆነም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የመሬት አጠቃቀም መረጃ (ጂኦስፓሻል) በማምረት ለተለያየ አገልግሎት የማብቃት ስራ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።

ኢትዮጵያ ላለፉት 65 አመታት የመሬት አጠቃቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ በማምረትና በማሰራጨት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም የመሬት አጠቃቀም መረጃ ለማከናወን የሚከናወኑ የአየር በረራ ስራዎች የሚከናወኑት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ነበር።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ አቅም እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።

አቅሙን ያሳደገው ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በምርምርና መረጃ አቅርቦት ስምምነቶችን አድርጎ እየሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የምርምር ስራዎችን የሚያግዙ የመሬት አጠቃቀም መረጃዎችን ግብዓቶችን ለማመንጨት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር ቱሉ ገለጻ፤ የጂኦስፓሻል መረጃ ፍላጎት በአገር አቀፍ ደረጃ እያደገ እየመጣ ነው።

በተለይም የግብርና ልማት እና የከተማ ልማት ስራዎች ከፍተኛ የሆነ የጂኦስፓሻል መረጃ ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ለማስፋትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ባሻገር መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ሶስት ማዕከላት መቋቋማቸውን ዶክተር ቱሉ ተናግረዋል።

በአየር ላይ ቅየሳ፣ በምድር ላይ ቅየሳና የተለያዩ ሳተላይት መረጃዎችን በማጠናከር መረጃዎችን ለማልማት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም