የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ብቃት ያለው የሠራዊት ግንባታ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል

93

አዲስ አበባ  መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለማንም ጠላት ሸብረክ ሳትል የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ብቃት ያለው የሠራዊት ግንባታ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።

የፌዴራል ፖሊስ በዛሬው ዕለት "ከራስ በላይ ለህዝብና ለአገር" በሚል መሪ ቃል በመስቀል አደባባይ የተለያዩ የሰልፍ ትርኢቶችን አቅርቧል።

የፌዴራል ፖሊስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋሙን ለማዘመን የተለያዩ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተከትሎ ነው በዛሬው እለት ያለበትን ቁመና እና አቋም የሚያሳይ ትርኢት ያቀረበው።

በዝግጅቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ለመላ የፖሊስ አባላት መልዕክት እና የሥራ መመሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በፖሊስ ተቋም ላይ የሪፎርም ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም ፖሊስ አገር ወዳድ፣ ህዝቡን አክባሪ፣ ራሱን ለህዝብና ለአገሩ አሳልፎ የሚሰጥ እንዲሆን ከማስቻል ባለፈ ከሚመጣውና ከሚሄደው ጋር የሚሄድ እንዳይሆን ተደርጎ መገንባቱን ተናግረዋል።

"ሁሌም ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር የሚጸና ሙያዊ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት ሲደረግ ለነበረው ጥረትም የዛሬው ትርኢት አንድ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛ ሆኖ ሁሌም ራሱን ከባንዲራ እና ከመለዮ ጋር አድርጎ በመርህ የሚሰራ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

"ሠራዊቱ በምቹ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ የአየር ፀባይ እንኳ ግዳጁን በብቃት መወጣት እንደሚችል የዛሬ ትርኢት አንዱ ማሳያ ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ።

ፖሊስ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ለሚያደርገው ጥረት መንግስት አስላጊውን ድጋፍ በማድረግ የተጀመረው የለውጥ ሥራ እንደሚጠናከርም አመልክተዋል።

"በመጨረሻም ኢትዮጵያ ለማንም ጠላት ሸብረክ ሳትል የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ብቃት ያለው የሠራዊት ግንባታ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ።

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ ዕለቱ ፖሊስ ለአገር ሠላምና ደህንነት ያለውን ሚና ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

"የሠላም ኃይሉ ዓላማውን በሚገባ የለየ ነው" ያሉት ሚኒስትሯ፣ የፖሊስ ተቋም ከቀደምት ታሪክ መልካም ነገሮችን ይዞ ማረም ያለበትን ደግሞ እያስተካከለ በሚጓዝበት ሁኔታ እየተደራጀና እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ፖሊስ የሕዝብ ሕልውና መሆኑን ጠቅሰው፣ ተልዕኮውን በአግባቡ መወጣት የሚችለው በአስተሳሰብና በአወቃቀር ከሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ሲችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የተጀመሩ የተቋም ግንባታ ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ያነሱት።

ሕዝቡም ይህን በመገንዘብ ከጸጥታ አካላት ጋር ለሠላሙና ለአገሩ ደህንነት በጥምረት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

ፓሊሰ እንደሁልጊዜው ሁሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሎ በብቃት ለመፈጸም በቂ ዝግጅት ማድረጉን የገለፁት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ናቸው።

የፌዴራል ፖሊስ ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረገለት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ተቋም መሆኑንም አስረድተዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር ተያይዞ ከግልፀኝነት እና ገለልተኝነት አኳያ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች በለውጡ ትኩረት ተሰጥቶት የማሻሻያ ሥራ እንደተሰራም ተናግረዋል።

በተለይ ጥናትን መሰረት ያደረጉ የሪፎርም ሥራዎች የተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በእዚህም ዘመናዊ፣ በእውቀትና በብቃት የጎለበቱ የፖሊስ ሠራዊት አባላትን ማፍራት እንደተቻለ አስረድተዋል።

በተቋሙ የተጀመረውን ለውጥ በየጊዜው በመፈተሽ፣ ጥንካሬዎችን በማጎልበትና ጉድለቶችን በማረም የተጀመረው ዘመን ተሻጋሪ ሙያዊ የፖሊስ ግንባታ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

ፖሊስ ህግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆም፣ የሚቃጡ ማናቸውም አይነት ጥቃቶችን ለመመከትና እርምጃ ለመውሰድ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን ለሰላሙ የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም