የኢሬቻ በዓል ከፖለቲካ የጸዳ በመሆኑ በበዓሉ ስፍራ ማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት መንጸባረቅ የለበትም-አባገዳዎች

476

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል ከፖለቲካ አመለካከት የጸዳ በመሆኑ ማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ መንጸባረቅ የለበትም ሲሉ የኦሮሞ አባገዳዎች ተናገሩ።

በዓሉን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሞ አባገዳዎች የፖለቲካ ፓርቲ አላፊና ተቀያሪ መሆኑን፤ የህዝቡ ባህልና ወግ ደግሞ ለዘላለም የሚቀጥል በመሆኑ የኢሬቻ በዓል ከፖለቲካ ጋር ቀላቅሎ ማየት እንደማይገባ ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓል ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት የጸዳ በመሆኑ ማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ መንጸባረቅ እንደሌለበትም ነው አባገዳዎቹ የተናገሩት

አስተያየት ሰጪዎቹ ኢሬቻ ከፖለቲካም በላይ መሆኑን ገልጸው፣ ስለበዓሉ አከባበር በአባገዳዎች በራሳቸው መወሰኑንና  መንግስትም ሆነ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ስለበዓሉ አከባበር እንደማይወስኑ አመልክተዋል።

በበዓሉ ሲከበር የሚንጸባረቅ የፖለቲካ አመለካከት ካለ በዓሉንና ባህሉን ስለሚያበላሽ በበዓሉ ተሳታፊዎች ዘንድ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክረዋል።

በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በተለይ የኦሮሞ ወጣቶች በሰከነ መንፈስና በዓሉ በሚፈቅደው ስርዓት መሰረት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡

ኢሬቻ የሚከበርበት ቦታ ሰላም ነው የሚሰበክበት፤ ፍቅር ነው የሚወደስበት ይላሉ አባ ገዳዎቹ።

እሬቻ በዓል ካለምንም የፖለቲካ ልዩነት ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ቦታ ነው እንጂ ጥላቻ የሚሰበክበት ቦታ አይደለም ይላሉ።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ነው፡፡

የክረምት ወራት አልፎ ጸደይ ሲመጣ የሚከበረው አንደኛው በዓል “ኢሬቻ ብራ” የሚባል ሲሆን በውሃማ ሥፍራዎች የሚከበር ነው።

ሌላኛው በበልግ ወቅት የሚከበረው “ኢሬቻ አርፋሳ” የተባለው በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በከፍታ ቦታዎች ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት እንደሆነ ይነገራል።