ጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻለ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ የጤፍ ዝርያዎችን እያስተዋወቀ ነው

63

ጎንደር መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) ጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በዝናብ አጠር አካባቢዎች የተሻለ ምርት የሚሰጡ ሁለት አዳዲስ የጤፍ ዝርያዎችን በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ፡፡

ማዕከሉ በ2012/13 የምርት ዘመን በምዕራብ በለሳ ወረዳ ሶስት ቀበሌዎች በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በጤፍ ዝርያዎቹ ያካሄደውን የቴክኖሎጂ ምርምር የመስክ በዓል በማዘጋጀት አስጎብኝቷል፡፡

በዚህ ወቅት የማዕከሉ ኃላፊ አቶ አስፋው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ''ቦሰት''እና ''ፀደይ'' ሁለት አዳዲስ የጤፍ ዝርያዎች በዝናብ አጠር አካባቢዎች በሄክታር እስከ 21 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡

በምዕራብ በለሳ ወረዳ ሦስት ቀበሌዎች በ32 ሄክታር ማሳ 15 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ዝርያዎቹን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በ2012/13 ምርት ዘመን እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊ አርሶ አደሮቹ በማዕከሉ በተደረገላቸው የሙያ ድጋፍ ታግዘው ካለሙት የጤፍ ሰብል በሄክታር እስከ 18 ኩንታል ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

የአካባቢ የጤፍ ዝርያዎች የሚሰጡት ምርት በሄክታር ከ8 ኩንታል የማይበልጥ እንደሆነም አመልክተዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዱአለም ሙሉ በዞኑ በዚህ የምርት ዘመን 78ሺህ ሄክታር መሬት በጤፍ ሰብል ተሸፍኗል ብለዋል።

ከለማው መሬትም አንድ ሚሊዮን 600ሺህ  ኩንታል በላይ የጤፍ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ከምርምር ማዕከላት የሚወጡ የጤፍ ዝርያዎችን በማስፋትም ለአርሶ አደሩ በፍጥነት እንዲደርሱ በማድረግ የጤፍ  ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራልም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የአካባቢ ዝርያ በመጠቀም በግማሽ ሄክታር ማሳቸው በሚያለሙት የጤፍ ሰብል ከሁለት ኩንታል የበለጠ ምርት አግኝተው እንደማያውቁ የገለፁት በወረዳው የወራህላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እናንየ ፈንታ ናቸው፡፡

ምርምር ማዕከሉ ያቀረበላቸውን የጤፍ ዝርያ በመጠቀም ካለሙት ግማሽ ሄክታር ማሳም እስከ 7 ኩንታል ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ወረዳ  አርሶ አደር ሲራጅ ዘውዱ በበኩላቸው እስከ ዛሬ ሲጠቀሙበት ከነበረው ዘር ማዕከሉ ያቀረበላቸው የጤፍ ዝርያ ለየት ያለ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የምርምሩ ማዕከሉ ያቀረበላቸውን የጤፍ ዝርያ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ማልማታቸውንና ከዚህም የተሻለ  ምርት እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

አርሶ አደር አለልኝ ስመኘው በሰጡት አስተያየተ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም ከአሁን ቀደም ጤፍ አልምቼ አገኝ የነበረው ምርት በሄክታር 7 ኩንታል ሲሆን ከአዲሱ ዝርያ ግን 12 ኩንታል ምርት እጠብቃለሁ" ብለዋል፡፡

ጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል  ባዘጋጀው የመስክ በዓል  ከወረዳው ሦስት ቀበሌዎች የተውጣጡ አርሶ አደሮች፣ የስራ ኃላፊዎችና የግብርና ባለሙያዎች ሲሳተፉ የአርሶ አደሮችም የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥም መካሄዱን  ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም