ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የበቆሎ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ ነው

130

ሀዋሳ ፣መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) በሽታንና የአየር ፀባይ ለውጥን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የበቆሎ ዝርያዎችን በኩታ ገጠም የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እያስተዋወቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት አስታወቀ።

በኢንስትቲዩቱ የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሄበን አርሲ ወረዳ በኩታ ገጠም የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እያስተዋወቀ ያለውን የተሻሻለ የበቆሎ ዝርያ በመስክ ምልከታ  አስጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ በወቅቱ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም መሰል የምርምር ሰርቶ ማሳያዎች የሚመረጡት ለክትትል ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች ብቻ ነበር።

ወረዳው ለዋና አስፋልት መንገድ የራቀ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ በቂ የምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ድጋፍ ሳያገኙ መቆየታቸውን አሰታውሰዋል።

ሁኔታው በግብርና ሥራ ሁሉም አካባቢዎች እኩል እንዳያድጉና  ሀገሪቱም ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።

"ኢንስትቲዩቱ ችግሩን ለመፍታት የበቆሎ ዝርያ ተደራሽ ያልሆኑባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎችን በመዳሰስ በወሰደው ተነሳሽነት በወረዳው የማላመድ ሰርቶ ማሳያ ተቋቁሟል" ብለዋል።

ሰርቶ ማሳያው በአርሶ አደሮች ማሳ መካሄዱ ልምዱን ወደ ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች በቀላሉ ለማድረስ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ልምዱን የማስፋፋት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በኢንስትቲዩቱ የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፊሊጶስ ማዕከሉ በመድኃኒትና መአዛማ ዕፅዋቶች እንዲሁም በተለያዩ ሰብሎች ላይ ምርምር በማካሄድ የተሸሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በአሮሚያና በደቡብ ክልል በቆሎ አምራች አካባቢዎች ላይ የአየር ፀባይ ለውጥን እንዲሁም ተባይና በሽታ ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የበቆሎ ዝርያዎችን እያስተዋወቀ መሆኑን ገልጸዋል ።

ማዕከሉ መልካሳ-2፣ ቢ ኤች 546፣ 547ና 549 የተሻሻሉ የበቆሎ ዝርያዎችን በምርምር በማዳቀል ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በኦሮሞያ ክልል ሄበን አርሲ ወረዳ በ60 ሄክታር ኩታገጠም የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የለማ “ ቢ . ኤች 546 ” የተሻሻለ የበቆሎ ዝርያ ድርቅን ተቋቁሞ በሄክታር ከ85 ኩንታል በላይ  ምርት መስጠቱን ተናግረዋል ።

በወረዳው እየተካሄደ ላለው ሰርቶ ማሳያ ማሳ ሙሉ የምርትና ምርታማነት ፓኬጅ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል ።

ሥራው በሰፊ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ መከናወኑ የቴክኖሎጂውን ተአማኒነት ከማረጋገጥ ባሻገር ልምዱን ወደ ሌሎች ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው አስረድተዋል።

ማዕከሉ በሌሎችም ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች ዝርያ የማስተዋወቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል  አስታውቀዋል።

የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር አቡ መገራ ከዚህ ቀደም ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ኩታ ገጠም በሆነ ማሳቸው ለሚያለሙት የበቆሎ ዝርያ ከመሬቱ በቂ እርጥበት ባለመገኘቱ ዝቅተኛ ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል ።

"አዲሱ የበቆሎ ዝርያ ከበፊቱ በተለየ መልኩ ድርቅን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት ይሰጠኛል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

ከዚህ በፊት ከሚዘሩት ዝርያ በሄክታር እስከ 35 ኩንታል ምርት ያገኙ እንደነበር የገለፁት አርሶ አደር ጉታ  ዘንድሮ ከዘሩት ዝርያ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል ።

አርሶ አደር ፈይሶ ቀርሺ በበኩላቸው ከማዕከሉ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልፀው ማዳበሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ ከባለሙያዎች በቂ ዕውቀት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

በማሳቸው እየተካሄደ ባለው የተሻሻለ አሰራር ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮችም ጭምር ልምድ መቅሰም መጀመራቸውንም ገልፀዋል።

 "የአካባቢው ሥነ-ምህዳር ለበቆሎ ምርት ምቹ ቢሆንም አርሶ አደሩ በተለያዩ ምክንያቶች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል" ያሉት ደግሞ የሄበን አርሲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በሪሶ ብሊዬ ናቸው።

ከማእከሉ ጋር በመተባበር ተሞክሮውን ወደ ሁሉም አርሶ አደሮች ለማድረስ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በመስክ ምልከታው የኢንስትቲዩቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የመንግስት አካላትና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም