ለቱሪዝም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ አገሪቱ ከዘርፉ እምብዛም ተጠቃሚ አይደለችም

52

አዲስ አበባ፣መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለቱሪዝም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ አገሪቷ ከዘረፉ እምብዛም ተጠቃሚ አለመሆኗ ተገለጸ።

ዓለም አቀፉን የቱሪዝም ቀን በማስመልከት ኢዜአ ከዘርፉ አካላት ጋር በሱባ መናገሻ ደን ውይይት አካሂዷል።

የዓለም የቱሪዝም ቀን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ41ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ "ቱሪዝም እና ገጠር ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

እለቱን በማስመልከት የዘርፉ አካላት ጋር ውይይት የተደረገበት የሱባ መናገሻ ደን ከ560 ዓመት በላይ ያስቆጠረና ከአፍሪካም በእድሜ ትልቁ ጥብቅ የደን ስፍራ እንደሆነ ይገለጻል።

ከአዲስ አበባ 46 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው እና 9 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የሱባ መናገሻ ደን 3 ሺህ 500 ሄክታሩ በደን የተሸፈነ ነው።  

በዚህ ጥብቅ የደን ስፍራ 186 የአእዋፍ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን 4ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ፣ 9ኙ ደግሞ በኢትየጵያና በኤርትራ የሚገኙ ናቸው።

በስፍራው 167 አይነት የዛፍ ዝርያዎች እና 32 አጥቢ እንስሳትንም መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

የሱባ መናገሻ ደን በኢትየጵያም የመጀመሪያው ችግኝ ማፍያ ጥብቅ ስፍራ እንደሆነም ይነገራል።

በኢትዮጵያ እነዚህን የመሳሰሉ ታሪካዊና ድንቅ ስፍራዎች ቢኖሩም ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም ያለውን ሃብት ያክል አለመሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይገልጻሉ።

ለዚህም በተለይ ለዘርፉ አስፈላጊ የሆነ የኢንቨስትመንት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አለመኖር ለዘረፉ ተጠቃሚነት ማነስ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

ለቱሪዝም ልማት ባለሃብቶችም ይሁኑ ሌሎች የማህበረሰብ አካላት ከከተሞች ባሻገር በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ መዳረሻዎች ላይ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው አናሳ መሆም ሌላኛው ችግር መሆኑን ገልጸዋል።  

አቶ ገዛሃኝ አባተ የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት የሱባን መንገድ ችግር መፍታት ቢቻልና ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራ ማህበረሰቡን ማንቀሳቀስና ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡

የአካባቢው አመራርም መንግስትን ሳይጠብቅ በአካባቢየ ምን አለ ብሎ ራሱን ቢጠይቅና  የአካባቢውን ጸጋ መለየት ቢችል ወጣቱን በዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል ገልጸዋል።

አቶ ናሆም አድማሱ የታላቁ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ባልታወቁና ትኩረት ባልተሰጣቸው አካባቢዎች ላይ ቱሪስቶች የሚጎበኙበት እንዲሁም ባለሃብቶች መዋዕለ-ነዋያቸውን አፍስሰው መስራት የሚችሉበት ሰፊ እድል ቢኖርም ቱሪዝሙን ማንቀሳቀስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ግን ብዙ አለመሰራቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይም በቱሪዝም ኢትዮጵያ በኩል ባለሃብቶች ወደ ገጠሩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰማርተው እንዲሰሩ ለማድረግ ፓኬጆች ተቀርጸው ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ስለሺ ገልጸዋል።

ለዚህም ሰባት ቦታዎች የተለዩ ሲሆን የባሌና የሰሜን ተራሮች፣ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም የአዋሽ፣ ኤርታሌና ገርአልታ አካባቢዎች ይገኙበታል።

በመሆኑም ባለሃብቶ በእንደነዚህ አካባቢዎች ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉ ከቀረጥ ነጻ ማበረታቻዎች በተጨማሪ የ5 አመት የግብር እፎይታ እንዲያገኙ የማድረግ ሁኔታዎች የሚመቻቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ስለሺ ግርማ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር በተለይ ባለሃብቶች ከከተሞች ወጥተው በገጠራማ አካባቢዎች ላይ መዋለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ራሳቸውንና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ እንዲሁም የአገሪቱንም ኢኮኖሚ እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም