በደቡብ ወሎ ዞን የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው…የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ

490

ደሴ  መስከረም 17/2013(ኢዜአ)በደቡብ ወሎ ዞን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ሃብት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የቱሪዝም ሃብቶችን ማልማት በሚቻልበት ዙሪያ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቅደላ አምባ ወረዳ ወይይት አካሒደዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ኃይሉ ታደሰ እንደገለጹት ወሎ በርካታ ታሪካዊ፤ ሐይማታዊና ባህላዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አሉት፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከዘርፉ የሚፈለገውን ያክል ጠቀሜታ ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸው በተለይም የመሰረተ ልማት ችግር በዘርፉ ከፍተኛ መሰናክል እየፈጠረ በመሆኑ ባለፉት አስር ዓመታት 15 ሺህ የውጭ ቱሪስቶች ብቻ አካባቢውን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።

ችግሮችን በማቃለል ዞኑን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከወሎና መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት መጀመሩን ገልጸዋል።

“በተለይ ጃማ ንጉስ፤ ግሸን ደብረ ክርቤ፤ ደገር ሸህዬ፤ ሐይቅ እስጢፋኖስ፤ ይስማ ንጉስ፤ ሸህ ሁሴን ጅብሪልና ሌሎች አካባቢዎችን በማልማት የቱሪስ መዳረሻ እንዲሆኑ ስራ ተጀምሯል”ብለዋል፡፡

“የጠፉ ቅርሶችን በማሰባሰብ፤ ሙዚየም በመገንባትና መሰረተ ልማቶችን በማስተካከል የገቢ ምንጭና የስራ እድል መፍጠሪያ በማድረግ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እንሰራለን” ብለዋል፡፡

በቅርሶች ላይ የሚደርሰውን ስርቆትና የመጥፋት አደጋ ለመታደግም በዘመናዊ ዲጂታል ዘዴ የታገዘ የቅርስ ምዝገባ መጀመሩን ጠቁመው ሲጠናቀቅ የተጠያቂነት አሰራር እንደሚሰፍንም አስረድተዋል።

የመቅደላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ሞላ በበኩላቸው እንደተናገሩት መቅደላ በርካታ በታሪካዊና ሐይማኖታዊ አካባቢዎች ቢኖሩም መልማት ባለመቻላቸው የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡

ዘጠኝ ከፍልፍል ድንጋይ የተገነቡ ቤተክርስቲያኖችን ጨምሮ የትንቢት ተናጋሪው ሸህ ሁሴን ጅብሪልን የትውልድ ቦታና የመቃብር ስፍራ ፤ የንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግስትና ጥንታዊ መስጅዶችም በዚሁ አካባቢ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“የቱሪዝም ሃብቱን ለመጠቀም ለጊዜው ያገጠመውን የመሰረተ ልማት ችግር ለማቃለል እየተሞከረ ቢሆንም ከአቅም በላይ በመሆኑ የክልልና የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን በጥናት በመለየት ለኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚደረግም የገለጹት የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን አህመድ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በቱሪዝም ሀብትና በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ 32 ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን አመልክተው “ሲጠናቀቁም ወደ ተግባር ይቀየራሉ” ብለዋል፡፡

የአካባቢው መገለጫ የሆነ የባህል ማዕከል ለመገንባትም መስከረም 24/2013 የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታ ለመጀመር መታሰቡን ጠቅሰዋል።

“ከቱሪዝም የሚገኘውን ሃብት በማሳደግና ቅርሶች፤ ባህልና እሴቶች ለትውልድ እንዲተላለፉ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን ይወጣልም” ብለዋል፡፡

የመቅደላ ወረዳ ነዋሪና የሸህ ሁሴን ጅብሪል 4ኛ ቤተሰብ ሸህ መውደድ ከበደ በበኩላቸው በዓለም የሚታወቁት ትንቢት ተናጋሪው ሸህ ሁሴን ጅብሪል የትውልድና የቀብር ቦታ ባለመከበሩ ቅር መሰኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

“በአካባቢው ያሉ የተለያዩ ሐይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶችም የሚንከባከባቸው፤ የሚጠብቃቸውና የሚጠግናቸው በማጣታቸው በመጥፋት ላይ ናቸው” ብለዋል፡፡

“በመሆኑም የሚመለከተው አካል ሁሉ የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን በመጠበቅ ለትውልድ እንዲተላለፉ መስራት ይገባል” ብለዋል።

በመቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ የደቡብ ወሎ ዞንና የመቅደላ አምባ ዩኒቭርሲቲ አመራሮች፤ ባለሙያዎች፤ የሐይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡