ሱዳናውያኑ ባለሀብቶች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት አላቸው

545

አዲስ አበባ መስከረም 17/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የሱዳን ባለሀብቶች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለጸ።

የሱዳን ባለሀብቶች ልዑካን ቡድን ትናንት ኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ሲገባ በክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮና በክልሉ የቱሪዝም ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች አቀባባል ተደርጎላቸዋል።

በጠቅላላ 22 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮችና የልማት ሥራዎች ለመመልከት መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ይታወቃል።

ቡድኑ ኦሮሚያ ክልል ከመግባቱ በፊት በአማራ ክልል የሚገኙትን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም የጎርጎራ አካባቢ የቱሪዝም አማራጮችን መጎብኘቱ ይታወቃል።

የልዑካን ቡድኑ መሪ ዶክተር ታግለዲን አብዱልጃሲም ባለሀብቶቹ በቱሪዝም መስክ የሚሰሩ እንደሆኑና በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪዝም አማራጮችን ለማየት ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

የሱዳን ባለሀብቶች ተፈጥሯዊ ሀብቶች በሚገኙባቸው ቦታዎች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

በጎርጎራ ባሉ የቱሪዝም አማራጮች ላይ ባለሀብቶቹ መዋዕለነዋያቸውን ለማፍሰስ እንደሚፈልጉም አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያ ጥሩ የአሰራር ሰርአት ከዘረጋችና ባሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች የመሰረተ ልማት ሥራዎች ላይ ማሻሻያ ካደረገች ይበልጥ የቱሪዝም ኢንቨስትመንትን መሳብ ትችላለች” ብለዋል ሚስተር ታግለዲን።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሌላ የሱዳን ባለሀብቶች የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ሚስተር ታግለዲን ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው የሱዳን ባለሀብቶች የልዑካን ቡድን በክልሉ በሚያደርጉት ጉብኝት በቱሪዝም ዘርፍ ያሉ መደረሻዎችን እንደሚመለከቱ ተናግረዋል።

“ባለሀብቶቹ በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታም የአብያታና ሻላ ሐይቆች፣ የአዋሽና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ” ብለዋል።

በቢሾፍቱ አካባቢ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሃብቶችንም እንደሚጎበኙም ገልጸዋል።

የባለሃብቶቹ ቡድን በኦሮሚያ ክልል እስከ መስከረም 21 እንደሚቆይና የክልሉን ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና የልማት ሥራዎችን እንደሚመለከትም አቶ ከበደ ጠቁመዋል።

ቡድኑ የኦሮሚያ ክልል ጉብኝቱን ሲያጠናቅቅ በደቡብ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይመለከታል ተብሎ ይጠበቃል።

የሱዳን ባለሃብቶች ቡድን የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮችና የልማት ሥራ ጉብኝቱን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቆይታውን መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።