በዓዲግራትና አክሱም ከተሞች የመስቀል በዓል ተከበረ

821

ዓዲግራት/ አክሱም መስከረም 17/13 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በዓዲግራትና አክሱም ከተሞች የመስቀል በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት ተከበረ።

በከተሞቹ ኮሮና ቫይረስ መከላከልን ታሳቢ ባደረገ መልኩ  በዓሉ መከበሩ ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያ የትግራይ ምስራቃዊ ዞን ሊቀጳጳስ አቡነ መራህ ክርስቶስ በአዲግራት ወልዋሎ ስታድየም በተከበረው በዓል ላይ  ባስተላለፉት መልዕክት መስቀል የብርሃን፣ የሰላም፣ ጽናትና የቤዛ በዓል ነው።

ምእመናን የመስቀል ቃልን በተግባር በማረጋገጥ አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

የትግራይ ክልል አፈ ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሽፋረ በበኩላቸው መስቀል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያለው ታላቅ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የበዓሉ ታዳሚዎችም “የመስቀል በዓል የሚያስተምረው ሰላምና ፍቅርን እንጂ ጥላቻና ፀብ እንዳልሆነ አውቀን ለሃገራዊ አንድነትና እድገት ልንጠቀምበት ይገባል” ብለዋል።

“የመስቀል በዓል የመተሳሰብና የአንድነት በዓል ነው” ያሉት ደግሞ በአክሱም ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶችና የበዓሉ ታዳሚዎች ናቸው።

የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ መርቆርዮስ  ምዕመናን የመስቀል በዓልን ሲያከብሩ መንፈሳዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“መስቀል የአንድነትና የቤተሰባዊነት በዓል በመሆኑ ያለው ለሌለው ወገኑ በማካፈል በዓሉን ማክበር ይገባል” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ሃፍቶም ኃይለአብ “ኢትዮጵያዊያን በመስቀል በዓል ለሀገራችንና ለወገኖቻችን ፍቅርንና መዋደድን በተግባር ልናሳይ ይገባል” ብለዋል።

“መስቀል የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር መገለጫ ነው” ያሉት አቶ ሃፍቶም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን የተቸገሩን በመርዳት በዓሉን አያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

“የመስቀል ደመራ በዓልም ለሀገራችን ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል ።

”መስቀል ፍቅርን፣ አንድነትንና ሰላምን የምናገኝበት ታላቅ በዓል ነው” ያሉት ደግሞ የበዓሉ ታዳሚ  ወይዘሮ ትዕግስቲ አፈወርቂ ናቸው።

የአክሱም ከተማ የህብረተሰብ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መምህርት አልማዝ ታደሰ በዓሉን ምክንያት በማድረግ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለ145 የተቸገሩ ወገኖች የምግብ እህልና የኮረና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል ።