የሕዳሴው ግድብ የሱዳን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው — የሱዳን ባለሀብቶች ልዑካን ቡድን መሪ

872

አዲስ አበባ መስከረም 17/2013(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሱዳን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የሱዳን ባለሀብቶች የልዑካን ቡድን መሪ ታግለዲን አብዱልጃሲም ገለጹ።

የግንባታ ሥራው በ2004 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል።

ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት በማይጎዳ መልኩና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በሚያሰፍን መልኩ እየተከናወነ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ ስትገልጽ ቆይታለች።

የሱዳን ባለሀብቶች የልዑካን ቡድን ከመስከረም12 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የልዑካን ቡድኑ መሪ ታግለዲን አብዱልጃሲም የሕዳሴ ግድብ ሱዳንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የገለጹት።

የሕዳሴው ግድብ የሁለቱን አገራት ህዝቦች በልማት የማስተሳሰር አቅም ያለውና የሁለትዮሽ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት በደም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸውም ነው ሚስተር ታግለዲን ያመለከቱት።

የልዑካን ቡድኑ መሪ ታግለዲን እንዳሉት ሁለቱ አገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ማድረግ ይገባቸዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን ከቱሪዝም ዘርፉ በተጨማሪ በጤናና በሌሎች መስኮች ትብብር በመፍጠር ግንኙነታቸውን ማጎልበት የሚችሉባቸው አማራጮች እንዳሉም ጠቁመዋል።

በራስ አቅም እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታው አፈጻጸም ከ75 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ግንባታውም በ2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።