በዓላት ሲከበሩ ለኮሮናቫይረስ የሚደረገው ጥንቃቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ

51

አዲስ አበባ መስከረም 17/2013 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል በጥንቃቄና በውስን ሰዎች ብቻ መከበሩ የኮሮናቫይረስ መዛመትን ለመከላከል በመሆኑ በቀጣይም በዓላት በተመሳሳይ ጥንቃቄዎች መከበር አለባቸው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች ተናገሩ።

ወቅታዊዩን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ሲባል እንደ ደመራ አከባበር ሁሉ ሌሎች ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትም በጥንቃቄ ሊከበሩ ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የደመራ በዓል አከባበር ላይ ያገኘናቸው መጋቢ አዲስ ሳሙኤል፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱ ለበዓሉ የመቀዛቀዝ ድባብ ቢፈጥርም የዛሬውን ክፉ ጊዜ አልፎ ነገን በደስታ ለመቀበል ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዲያቆን ታደሰ ካሳም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል መዘናጋትን በመተው ሁሌም መጠንቀቅ ይገባል ብለዋል።

"የመስቀል በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ በውስን ሰዎች መከበሩ የክብረ በዓሉን ድባብ ያቀዛቀዘው ቢመስልም መስቀል የአብሮነታችን ማሳያ ስለሆነ በደስታ እያከበርነው ነው" ያሉት ደግሞ ሊቀ ዲያቆን ሰለሞን ጥላሁን ናቸው፡፡

በዓሉ እንደከዚህ ቀደሙ በርካታ ሰዎች ባይሳተፉበትም ባለውና በተፈቀደው ሰው ልክ በዓለ መስቀሉ በደስታ እየተከበረ መሆኑን የበዓሉ ታዳሚ የሆኑት መባ-ጺዮን ስለሺ ናቸው።

በቀታይ ዓመት "ኮሮና ይጠፋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ" ያሉት አስተያየት ሰጭው የተጀመረው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትም ተጠናቆ እንድናከብረው "ሰላማችንን እያስጠበቅን ልማታችንን ማስቀጠል" አለብን ብለዋል።

መምህር መክብብ ገበረ ማርያም በበኩላቸው ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ማሸነፍ የሚቻለው የጥንቃቄ መመሪያዎችን በማክበር መሆኑን ገልጸዋል።

የበለጸጉ አገራት ባለቸው የህክምና ባለሙያ ብዛት መቋቋም ያልቻሉትን ወረርሽኝ እኛ መከላከል ያለብን በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ብቻ እንደሆነም መክረዋል፡፡

ሊቀ ዲቆን ሰለሞን ጥላሁንም "ነገን ለመኖር የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ግድ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም