የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ መሻሻል የሚና ክፍፍል ክንውን በአግባቡ እንዲሆን ይረዳል- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

514

አዲስ አበባ መስከረም 17/2013(ኢዜአ) የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ መሻሻሉ በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚና እና የኃላፊነት ክፍፍል በአግባቡ እንዲከናወን የሚረዳ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ1954ቱ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

የግልግል ዳኝነትን እና የዕርቅ አሠራር ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ ደንብን ጨምሮ በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዐበይት ውሳኔዎችን ማሳለፉንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ገልጸዋል።

የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጁ መሻሻሉ በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚና እና የኃላፊነት ክፍፍል በአግባቡ እንዲከናወን የሚረዳ ወሳኝ ርምጃ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 90ኛ መደበኛ ስብሰባው እንዲፀድቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመራቸው የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ስርዓት ረቂቅ አዋጅና የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓትና የማስረጃ ሕግ ሥነ ስርዓት ማሻሻያ አዋጅ ላይ ትናንት ማብራሪያ ሰጥቷል።

በስራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በ1954 የተቀረፀ፣ አሃዳዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዓትን የተከተለና አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ስርዓት ያላገናዘበ መሆኑም በዚሁ ጊዜ ተብራርቷል።

የተሻሻለው ሕግ የተከሳሾችን መብት ከመጠበቅ ባሻገር የፍርድ ቤቶችን አሰራር ማቀላጠፍ የሚያስችል መሆኑም ተመልክቷል።

የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ሥርዓት አዋጁም ከመደበኛው የዳኝነት ሥርዓት ተጨማሪ አማራጭ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑም ተብራርቷል።

በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑም መገለጹ ይታወሳል።