በግሸን ደብረ ከርቤ በዓል ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደረገ

108

ደሴ መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) በግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ኮሮናን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያና ሃገረ ስብከት አስታወቁ፡፡

የመምሪያ ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ ለኢዜአ እንደገለጹት በየዓመቱ መስከረም 21 የሚከበረው የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ በዓል  በርካታ ህዝብ የሚታደምበት ነው፡፡

ከዚህ በፊት ከሁለት ሚሊዮን በላይ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች ይሳተፉበት እንደነበረ  አስታውሰው  ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተሳታፊዎች ቁጥር እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

ኮሮናን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በበዓሉ ለመታደም የሚመጡ የተወሰኑ እንግዶችን ለማስተናገድ ከወዲሁ  ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከል  የትራንስፖርት መንገድ  ጠረጋ፣  መጸዳጃ ቤት፣ ተሸከርካሪ ማቆሚያ፣ መመገቢያ አዳራሽና  የጤና አገልግሎት መስጪያ ይገኙበታል።

የውሃ እጥረት እንዳይከሰትና የመብራት መቆራረጥ እንዳይፈጠርም በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤  በተለያዩ አካባቢዎች የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች መመቻቸታቸውን አስታውቀዋል።

ምዕመናኑ ያለ ስጋት ደህንነቱ ተጠብቆ የመጣበትን ዓላማ ብቻ እንዲያሳካ ከአጎራባች ዞኖች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው ፤ መጓጓዣ ትራንስፖርት ችግር እንዳይፈጠርም ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

ለእንግዶችም የወሎ መገለጫ የሆኑ ባህላዊ ምግቦችና አልባሳት  በማቅረብ ያለውን አንድነት፣ ሰላምና የፍቅር ተምሳሌት በሌሎች አካባቢዎችም እንዲሰፋ ዞኑ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ መምህር ብርሃነ ሕይወት እውነቱ በበኩላቸው ክብረ በዓሉ  ለኮሮና መከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

ለምዕመናኑ ግንዛቤ የሚፈጥር ትምህርት፣ የአፋና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የሚያስለብሱ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ የሚያቀርቡና የሚያስተባብሩ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡

ሆኖም  የተሳሳተ አመለካከት ያላቸውና የጥፋት ተልኮ የሚያራምዱ ስለሚኖሩ ለመከላከል ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

"ማንኛውም አማኝ ጥንቃቄ ማድረጉ የእምነቱ አንድ አካል ነው "ያሉት ሊቀ መምህሩ ወደ ክብረ በዓሉ የሚመጣ ሁሉ ጭንብልና  የንጽህና መጠበቂያ  ቁሳቁሶችን መያዝ እንደሚጠበቅበትም አስታውቀዋል፡፡

በዓሉ በሰላም እንዲከበርም ከደቡብና ሰሜን ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ፣ ሰሜን ሸዋና ሌሎች አካባቢዎች ካሉ የአስተዳደር አካላት ፣ ኃይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ እንዳያስከፍሉ፣ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ፣ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት፣ መተፋፈግና መጨናነቅ እንዳይፈጠርም እየተሰራ ነው፡፡

ምዕመናኑ ከመስከረም 13 ጀምሮ ወደ ቦታው መግባት በመጀመሩ የእንግዶች ማረፊያ፣ መመገቢያ አዳራሽ፣ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያና የችሎት ቦታ ተመቻችቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

በዓሉ ከተለያየ አቅጣጫዎች የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን   የሚያገናኝ በመሆኑም አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንዳለውም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም