የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው ግጭቶች ተሳትፈዋል በተባሉ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቷል

50

 አዲስ አበባ  መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች ተሳትፈዋል በተባሉ 5 ሺህ 728 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለፀ። 

ተከሳሾቹ የእርስ በእርስ ግጭት በማነሳሳትና በሽብር ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ተገልጿል።

የፌዴራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ፀጋ እንደገለፁት የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈፀመ የወንጀል ድርጊት ዙሪያ ምርመራ ሲካሄድ ቆይቷል።

ምርመራው ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በጋራ መካሄዱን ነው የገለፁት።

ተከስቶ በነበረው ሁከት የ167 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ 360 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንና ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን አብራርተዋል።

በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፈዋል በተባሉ 5 ሺህ 728 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱንም ገልፀዋል።

አብዛኞቹ ተከሳሾች በወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 የእርስ በእርስ ግጭት በማነሳሳት፤ 63 ሰዎች ደግሞ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው እንደሆኑም ገልጸዋል።

ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታ ሰፊና የተራራቀ መሆኑና የደረሰውም ጉዳት መብዛቱ ምርመራው ላይ በተወሰነ መልኩ አዳጋች ሁኔታ መፍጠሩንም አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተካሄደው ምርመራ በአብዛኛው መጠናቀቁን የገለፁት አቶ ፍቃዱ አነስተኛ የወንጀል ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎች ጉዳይም በቀጣዩ ሳምንት ይጠናቀቃል ብለዋል።

በወንጀል ምርመራ ሂደቱ ትብብር ላደረጉ የፍትህና የፀጥታ አካላት፣ የክልልና የከተማ አመራሮችና ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።

በምርመራ ሂደቱ ተሳታፊ የነበሩ ምስክሮች አሁንም ትብብራቸውን እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

በፌዴራል ደረጃ በአዲስ አበባ እየታዩ ያሉት በእነ አቶ እስክንድር ነጋና አቶ ጃዋር መሀመድ መዝገብ ስር ያሉ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሆነም ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም